የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው ተቃውሞ መፍትሄን እንዲያገኝ ሃሙስ ጥሪ አቀረበ

ኢሳት (ነሃሴ 5 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለው ተቃውሞ ያለምንም መዘግየት በሰላማዊ መንገድ መፍትሄን እንዲያገኝ ሃሙስ ጥሪውን አቀረበ።

በተለይ ከቀናት በፊት በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በተፈጸሙ ግድያዎች ስጋት እንዳደረበት የገለጸው ህብረቱ ተጨማሪ ሁከትና ግጭት ለሰላማዊ መፍትሄ እንቅፋት እንደሚሆን አስታውቋል።

በሁለቱ ክልሎች ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ግድያ ምክንያት የሆነውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ መግለጫን ያወጣው የአውሮፓ ህብረት ለተነሱ ቅሬታዎች አሳታፊ መፍትሄዎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

የአውሮፓ ህብረት ከወራት በፊት በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ መንገድ የተፈጸመውን የሰዎች ግድያ በአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚቴን ጨምሮ አሜሪካና የተለያዩ አለም አቀፍ አካላት በሃገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በአስቸኳይ እልባት እንዲያገኝ በማሳሰብ ላይ ናቸው። የሃገሪቱ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለወራት የዘለቀው ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበት በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄን ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር እንደሚያደርግ ገልጿል።

ከአለም አቀፍ አካላት እየቀረበ ላለው ጥያኣቄ ምላሹን የሰጠው መንግስት አለም አቀፍ መርማሪ ቡድን ሃገሪቱ መስማቱን አስፈላጊም አይደለም በማለት ትግብብር መንፈጉን አልጀዚራ የቴሌቪዥን ጣቢያ ሃሙስ ዘግቧል።