ህወሃት በበላይነት የሚመራው መንግስት በብሄረሰቦች መካከል መቃቃር እንዲፈጠር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 5 ፥ 2008)

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሰላማዊ ሰልፈኞች በተለያዩ ጊዜያት ባደረጓቸው ህዝባዊ ተቃውሞች በአገሪቷ ለተፈጠረው ቀውስ የህወሃትን አመራር ተጠያቂ ነው ቢሉም፣ ስልጣን ላይ ያለው የህወሃት ቡድን በበኩሉ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የትግራይ ህዝብን በጅምላ ኢላማ ያደረጉ ናቸው በማለት በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ ክስ እያቀረበ እንደሚገኝ በአሜሪካ አገር ዋሽንግተን ዲሲ የሚሰራጨው ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ (NPR) የተባለ ጣቢያ በረቡዕ ስርጭቱ ገለጸ።

በኦሮሚያና በአማራ ክልል ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩት ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ በፌዴራል መስሪያ ቤቶች ጨምሮ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን የሚቆጣጠሩትና የስራ ዕድል የሚያገኙት (የሚሰጣቸው) የህወሃት አባላት መሆናቸውን ገልጸው፥ የጸጥታና ደህንነት፣ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ተቋማት ጭምር እንዲሁ በህወሃት ሰዎች ተጨምድደው መያዛቸውን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን ዘግበዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በኦሮሚያ በተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች በአገሪቷ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር፣ የገበሬዎች መሬት ያለአግባብ እንዳይወሰድ፣ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄዎች መቅረባቸውን NPR በዘገባው አስታውቋል።

ከሳምንት በፊት በጎንደርና በባህርዳር “ወያኔ ከእንግዲህ አይገዛንም” ፣ “ወልቃይት አማራ ነው”፣ “በኦሮሚያ ክልል ያለው ግድያ ይቁም” ፣ “በመብታችን አንደራደርም” የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ የነበሩት ሰልፈኞች መንግስት በህዝቡ ላይ የሚያደርገውን አፈና እንዲያቆም መጠየቃቸው ይታወሳል።

በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ “ነጻነት እንፈልጋለን፣ የፖለቲካ እስረኞችን ይለቀቁ” በማለት መፈክር ሲያሰሙ እንደነበሩና፣ በመጨረሻም ሰልፉ በፖሊስ ሃይል መበተኑን ኢሳት ዘግቧል።ባለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ በኦሮሚያና አማራ ክልል ከተሞች ሰላማዊ ሰልፈኞች ሰልፉ እንዳይካሄድ በመንግስት የተላለፈን ውሳኔ በመጣስ አደባባ መውጣታቸውን ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ዘውግ ነው፣ ዘውግ ደግሞ ክልል ነው ያለው የNPR ዘገባ፣ በዘውግ ላይ የተመረኮዘ አከላለል አወዛጋቢ ከመሆኑም ባሻገር ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚህ በዘውግ የፖለቲካ መስመር እንዲደራጁ አድርጓቸዋል ብሏል። በመንግስት ላይ የሚቀርበው ማንኛውም ትችትም በዘውግ የፖለቲካ መስመር እንደሚፈረጅ የሬዲዮ ጣቢያው አትቷል።

በመሆኑም በዘውግ ፖለቲካ በምትናጥ አገር ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ችግር መግለጽ አገሪቷን “የጦር አውድማ” አድርጓታል በማለት የዜና አውታሩ በአገሪቷ እየተከሰተ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚና አስተዳደራዊ ችግሮችን በዘገባው ዳስሷል።

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተቀጣጠለ ያለውን ህዝባዊ ንቅናቄና የኢህአዴግ/ህወሃት አመራር እየወሰደ ያለውን የጅምላ ግድያ እርምጃ ኤን ፕ አርን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በከፍተኛ ሁኔታ ሽፋን እየሰጡት ይገኛሉ። ቢቢሲ፣ አልጀዚራ፣ ዩናይትድ ፕሬስ ኢንተርናሽናል፣ ኢንተርናሽናል ቢዝነስ ታይምስ፣ ዶቼ ቬለ፣ ሲ ኤን ኤን፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ሮይተርስ፣ ኸፊንግተን ፖስት፣ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ፣ አሶሽየትድ ፕሬስ እና ሌሎች በርካታ የዜና አውታሮች በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ እምቢተኝነትን ከዘገቡት አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ይጠቀሳሉ።

የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ሰፊ ዘገባን ተከትሎም የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሳምንቱ መገባደጃ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ማጣራት እንዲደረግበት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ረቡዕ ይፋ አድርጓል።