በ ምስራቅ በለሳ ወረዳ አምቦ በር ( እብናት) አካባቢ የጎንደር ከተማ ሰልፍ ከመካሄዱ ከሰአታት በፊት የፖሊስ ጣቢያ መጋዝን ተሰብሮ ከ12 በላይ ክላሽንኮቭ ጠመንጃዎች ፣ የፖሊስ ልብሶችና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ተዘርፈዋል።
ይህን ተከትሎ የከተማው የፖሊስ አዛዥ ትናንት አሰሳ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪ የተቃውሞ ሰልፍ ሲወጣ ታግዷል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ሃይሎች እነማን እንደሆኑ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ በዚህ አካባቢ ከወር በፊት ማንነታቸው ያልታወቁ ሃይሎች በፈጸሙት ጥቃት 6 ፖሊሶች መገደላቸው ይታወቃል። የአሁኑ ድርጊት ከዚሁ ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በቅርቡ በሰሜን ምእራብ እዝ ውስጥ የተካሄደውን ግምገማ ተከትሎ በርካታ ወታደሮች መጥፋታቸው ታውቋል።
ይህን ተከትሎ አስቸኳይ ግምገማ የተካሄደ ሲሆን፣ ወታደሮቹ የጠፉት ደሞዝ ስላለነሳቸው በማለት በግምገማው ላይ የተገኙ ወታደሮች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ይሁን እንጅ ግምገማውን የመሩት ኮሎኔሉ፣ ይህ የማይታመን ነው። የደሞዝ ጥያቄ ቀድሞ የነበረ ነው፣ ወታደሮቹ የጠፉት ግን አሁን ነው፤ እስከዛሬ ሳይጠፉ አሁን መጥፋታቸው ሌላ ነገር አለና አውጡ ብለው ወታደሮችን ቢያፋጥጡም፣ የተለየ መልስ ሊያገኙ አልቻሉም።
ጉዳዩ እያወዛገበ መሄዱን ተከትሎ ችግሩን አጥንቶ ለበላይ አዛዥ የሚያቀርቡ የኮሚቴ አባላት ተመርጠው ስብሰባው ተጠናቋል።
በባህርዳር መኮድ የሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት በህዝብ ላይ አንተኩስም፣ ለፖለቲካ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሄ ይሰጥ የሚሉ አቋሞችን ይዘዋል። “አገዛዙ መምራት ሲያቅተው እኛን ከህዝብ ጋር ለማጋጨት እየሰራ ነው” በማለት የቻሉት እየጠፉ ነው። ይህን ተከትሎ አጠቃላይ የሰራዊት ብወዛ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።