ኢሳት (ሃምሌ 25 ፥ 2008)
ስድስተኛውን አመታዊ ፌስቲባል በዋሽንግተን ዲሲ ጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ ያካሄደው “የኢትዮጵያውያን ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ” እውቅናውን የሰጠው በአርአያነት ተምሳሌት ለሆኑ እና ከራስ በላይ ለህዝብ መስዋዕት የሆኑትን በመምረጥ እንደሆነ አዘጋጁ ኮሚቴው አሳውቋል።
በተምሳሌታዊ አርዓያነት የክብር ዕውቅና የተሰጣቸው ዶ/ር ብሩክ ተድላ ከልጅነት እስከ እውቀት ለትምህርታቸው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የላቀ ውጤት በማስመዝገባቸው የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
ዶክትሬታቸውን በፊዚክስ እና ኢንጂነሪንግ የጨረሱት ዶ/ር ብሩክ ተድላ በሚያስመዘግቡት ከፍተኛ ውጤት ምክንያት የነጻ የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) በማግኘት መማራቸው ለእውቅና እንዳበቃቸው በአዘጋጅ ኮሚቴው ተገልጿል።
የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ በማስከተል እውቅና የሰጠው ለክቡር አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ነው። አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ከ60 አመት በላይ በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት እንዲከበር ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ እውቅና እንድታገኝና ድምጿ እንዲሰማ በማድረጋቸውና በልማት ያደረጉት አስተዋፅዖ እንደሆነ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ “ከራስ በላይ ለህዝብ መስዋዕት በመሆን” በማለት የክብር እውቅና የሰጠው ለአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የህይወት ዘመኑን በሙሉ ለነጻነት፣ ፍትህና ሰብዓዊ መብት መከበር የታገለ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑን ምስክርነት የሰጡት የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚደኣንት ብርሃነ መዋ፣ “የአንዳርጋቸው ስራ ዘወትር በኢትዮጵያውያን ይታወሳል” በማለት ገልጸዋል። ሽልማቱን ለአቶ አንዳርጋቸው ቤተሰቦች ያስረከበችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ በበኩሏ፣ “ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቱ ትውልድ አንዳርጋቸው የተነሳበትን አላማ ከፍጻሜ ማድረስ ታሪካዊ አደራ ተጥሎብናል” በማለት ገልጻለች። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት ነጻነታችንን እስክናረጋግጥ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝባለች።