ራሳቸውን ባቃጠሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ድርጊት ማዘኑን የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ገለጸ

ኢሳት (ሃምሌ 25 ፥ 2008)

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ ሰሞኑን ራሳቸውን ባቃጠሉ ሁለት ኢትዮጵያውያን ድርጊት ማዘኑን ገለጸ።

በተባበሩት መንግስታት የስደኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ የህዝብ መረጃና ኮሚውኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት ታሪክ ኣርጋዝ፣ በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጠረው ሁኔታ እጅግ አዝነናል ሲሉ ዴይሊ ኒውስ ኢጂይፕት ለተባለ ጋዜጣ ገልጸዋል። UNHCR

ሰዎቹ ራሳቸውን በእሳት ባቃጠሉበት ጊዜ ሶስት ሰዎች ተጎድተው እንደነበርና አንድ ሴት ሌላው ሰው ሲቃጠል ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ እራሳቸው በእሳት መያያዛቸውን ሚስተር ታሪክ አርጋዝ ገልጸዋል።

ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን በራፍ ራሳቸውን ካቃጠሉት ሁለት ኢትዮጵያውያን መካከል ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ አስሊ ኑሬ በደረሰባቸው ቃጠሎ ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ በመቅረታቸው ባለፈው ሳምንት ህይወታቸው አልፏል።

ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን በማቃጠል ተቃውሟቸውን የገለጹት፣ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን የካይሮ ቢሮ የስደተኝነት ጥያቄያቸው ውድቅ በማድረጉ እንደሆነም ቢነገርም፣ ችግሩ የተፈጠረው በግብፅ የስደተኞች ቁጥር በመጨመሩ ውሳኔ ለመስጠት ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ነው ሲሉ ሚስተር አርጋዝ ተናግረዋል።

ስደተኞቹ በማመልከቻው ሂደት ተስፋ መቁረጥ እንደሚታይባቸው የገለጸው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ፣ መዘግየቱ የተፈጠረው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች በመኖራቸው ነው ሲል በመግለጫው አውስቷል።

በትውልድ አካባቢ በመመርኮዝ የሚሰጥ ወይም የሚከለከል ጥገኝነት አሰጣት እንደሌለ የገለጸው የተመድ የስደተኞች ኮሚሽን የመረጃና ኮሚኒኬሽን ሃላፊ፣ ውሳኔውም በህግ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል። በቅርቡም በቂ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎች ጥገኝነት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

በቅርቡ ኦሮሚያ ከተካሄደው መጠነ ሰፊ ግድያ፣ ድብደባ፣ አፈናና እስራት ሸሽተው ግብጽ መድረሳቸው የተገለጸው ብዛት ያላቸው የኦሮሞ ክልል ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ በግብፅ ካይሮ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የጥገኝነት ጥያቄ ቢጠይቁም፣ ጥያቄያቸው ውድቅ በመድረጉ ብዙዎች በባህር ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሚያደርጉት ጉዞ ህይወታቸው እያለፈ እንደሆነ ይታወቃል።