በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ህዝባዊ ተቃውሞች እየተካሄዱ ነው

የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን የድምጻችን ይሰማ ተከትሎ የተጀመረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወደ ኦሮምያ ተሸጋግሮ የበርካታ ንጹሃን ዜጎችን ህይወት ከቀጠፈ በሁዋላ፣ ተቃውሞው ወደ ሰሜን በማምራት በሰሜን እና ደቡብ ጎንደር በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል። በህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት ላይ የተጀመረው ተቃውሞ አገራዊ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱንና በመሃል አዲስ አበባም በቅርቡ ህዝባዊ ተቃውሞች ሊደረጉ ይችላሉ የሚል ግምገማ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ማድረጉን መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል።

ትናንት በጎንደር ከተማ በ100 ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ተገኝቶ ባደረገው የተቃውሞ ሰልፍ የውልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የኮሚቴ አባላት እንዲሁም ታስረው የሚገኙት ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ እንዲፈቱ ጠይቋል። ህዝቡ ከእንግዲህ በከፋፍለህ ግዛ የህወሃት ፖሊሲ እንደማይገዛ በአደባባይ ተናግሯል። “የህወሃት አገዛዝ ያብቃ!” ሲል የህወሃት መስራች አባት የሚባሉትን የአቶ ስብሃት ነጋን ፎቶ በህይወት እያሉ በማቃጠል ተቃውሞውን ገልጿል። ህዝቡ በኦሮምያ  አካባቢዎች ለሚደረጉ ተቃውሞዎች ድጋፉን ሰጥቷል። የድምጻችን ይሰማ የኮሚቴ አባላት እንዲፈቱም ጠይቋል። ወጣቱ ይህ ታሪክ የምንሰራበት ዘመን ነው፣ ከእንግዲህ በባርነት አንኖርም፣ ዲሞክራሲያዊ መብታችን ይከበር የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን አሰምቷል።

የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት በጎንደር የሚካሄደው ሰልፍ እውቅና አላገኘ በመሆኑ መካሄድ የለብትም ሲል አሳስቦ ነበር። በህዝቡ ላይ ሽብር ለመልቀቅ ሰራዊቱን ከእያቅጣጫው አሰማርቶ ነበር። ከደቡብ ጎንደር፣ ከደሴና ከባህርዳር አካባቢ ወደ ሰልፉ ለመጓዝ የፈለጉ ሰዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች በሚደረግ ፍተሻ ጉዞአቸውን እንዲሰናከል ሆናል።

የጎንደር ህዝብ በገዢው ፓርቲ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ከቁብ ባለመቁጠር ወደ አደባባይ ገንፍሎ የወጣው ከጠዋት ሲሆን፣ የመንግስት ታጣቂዎች የህዝቡን ሁኔታ ሲያዩ ወደያው ጥግ ጥጋቸውን በመያዝ ሰልፉ እንዲካሄድ ፈቅደዋል። የጸጥታ ሃይሎች እርስ በርስ ተከፋፍለው የነበረ ሲሆን፣ የጦር መሳሪያ የያዙ ሰልፈኞች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመምጣት ዳር ዳር ቦታ ይዘው አድፍጠው በመጠባበቅ፣ የመንግስት ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ እንድ እርምጃ ለመውሰድ ቢሞክሩ ሊበቀሉዋቸው ተዘጋጅተው ነበር። ሆኖም ሁኔታው ያስፈራቸው አጋዚዎች እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ያልተፈቀደ ሰልፍ ደም ሳይፈስ፣ የታሰረ ሰው ሳይኖር ተጠናቋል።

የገዢው ፓርቲ የመገናኛኢ ብዙሃን ሰልፉ ከተካሄደ በሁዋላ፣ “በጎንደር ከተማ ከክልሉ መንግስት እና ከከተማ አስተዳደሩ ህጋዊ ፍቃድ ያለተጠየቀበት ሰልፍ ተካሂዷል።” ሲሉ ዘግበዋል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁንን  በመጥቀስ በሰልፉ ላይ “ የሀገሪቱ ሰንደቅ አለማ ያልሆኑ አርማዎችን ከመያዝ ጀምሮ ሌሎች ህገ መንግስቱን የጣሱ እና የሀገሪቱን አንደነት የመሸርሸር አላማ የነበራቸው ጥያቄዎች እና ድርጊቶች “ መታየታቸውን ገልጸዋል። እነዚህ የኢትዮጵያን አንድነት ይሸረሽራሉ ያሉትን ግን ህዝብ ግንኙነቱ አላብራሩም። ምንም እንኳ ቃል አቀባዩ ይህን ቢሉም ፣ የጎንደር ህዝብ የኦሮምያን ህዝብ ትግል በመደገፍ አጋርነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን ማሳየቱን በሰልፉ ላይ የተገኙት ሁሉ የመሰከሩት ጉዳይ ነው። በአንድም ኢትዮጵያዊ ላይ ጉዳት ሳይደርስ ገዢው ፓርቲ በተለይም ህወሃት ተለይቶ ውግዘት የደረሰበት መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ህወሃት ደግሞ የትግራይን ህዝብ አይወክልም ሲሉ ይከራከራሉ።

በጎንደር ተቃውሞ በመካሄድ ላይ እያለ የእስቴ ወረዳ ነዋሪዎች የፖሊሲን ማስፈራሪያና ጥበቃ ወደ ጎን በማለት የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በእስቴም እንዲሁ የወልቃይ ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ የተጠየቀ ሲሆን፣ ወጣቱ ከዚህ በተጨማሪ ለውጥ እንፈልጋለን ብሎአል። ወጣቱ የ25 አመታት አገዛዝ ይብቃ! የሌሎች አካባቢ ተወላጆችም ተነሱ! በማለት እየጮኸ እየሸለለ ተቃውሞውን አካሂዷል። በሚቀጥለው ሳምንት ተመሳሳይ ተቃውሞ በመካነ እየሱስ ለማካሄድ ኮሚቴ ተዋቅሯል።

ሰማያዊ ፓርቲም እንዲሁ በባህር ዳር ከተማ  የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የማሳወቂያ ደብዳቤ አስገብቷል። ፓርቲው ነሐሴ 01 ቀን 2008 ዓ/ም ለሚያካሂደው የተቃውሞ ሰልፍ ከሀሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2008 ዓ/ም ጀምሮ የባህር ዳር ከተማ

ከንቲባ ጽ/ቤትን  ምላሽ ሲጠብቅ ቆይቶ ባለማግኘቱ ፣  ሐምሌ 25 ቀን 2008 ዓ/ም ለባህርዳር አስተዳደር ከንቲባ ፅ/ቤት፣ ለፖሊስ እና ለፀጥታ ዘርፍ ደብዳቤ አስገብቷል።

ሰልፉ የፊታችን እሁድ በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል።

በርካታ የብአዴን ታጣቂዎች እና መከካለኛ ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች የህዝብን ትግል እየደገፉ መምጣታቸውን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። የደህንነት መስሪያ ቤቱ ተቃውሞው አዲስ አበባን ጨምሮ  በመላ አገሪቱ ይቀጣጠላል የሚል እምነት ላይ መድረሱን ምንጮቻንን አክለው ተናግረዋል።