ህዳር 7 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አቶ መለስ ፦” የታሰሩት ሰዎች በሙሉ ሽብርተኛ ለመሆናቸው ከበቂ በላይ ማረጋገጫ አለን” ሲሉ ቢደመጡም ፤የ ኢትዮጵያ ህዝብ ግን የታሠሩት በሙሉ የሰላምና የነፃነት ታጋዮች እንጂ አሸባሪዎች እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ሲናገር መቆየቱ ይታወቃል።
ከእስረኞቹ ቤተሰቦች አንዱ ለ ኢሳት በሰጡት አስተያዬት፦” የታሰሩት ወንድምና እህቶቻችን አሸባሪዎች እንዳልሆኑ ራሳቸው እነ አቶ መለስ ያውቁታል።የሚያደርጉት የትግል እንቅስቃሴ ስልጣናቸውን
እንዳያሳጣቸው በማሰብ ነው ያሰሯቸው። በጣም የሚገርመው ግን ነገር እነሱ ቢታሰሩም ፤ትግሉና ብሶቱ እየጠነከረ እንጂ እየተዳከመ አለመምጣቱ ነው”ብለዋል።
ትናንት ረቡዕ ደግሞ አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ናትናዔል ፍርድ ቤት ቀርበው ለሚቀጥለዉ እሮብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
በሚቀጥለው ረቡዕ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ዐቃቤ ህግ እነሱን ጨምሮ በሌሉበት በዚያው መዝገብ የተከሰሱ የ24 ሰዎችን ምስክርና ማስረጃ ማቅረብ እንደሚጀምር ታውቋል።
አቶ አንዷለም፣ አቶ ናትናኤል እና ጋዜጠኛ እስክንድር የተመሰረተባቸዉን ክስ ባቆሙት ጠበቃ አማካይነት ለመከላከል መዘጋጀታቸውም ታውቋል።
የአቶ መለስ መንግስት በነአቶ አንዱዋለም አራጌ ላይ፦” የግንቦት ሰባት አባላት ናቸው፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር በማበር መንግስትን ለመጣል እየተንቀሳቀሱ ነው። አገራዊ መረጃዎችን ጠላት ለሆነው
ለኤርትራ መንግስት አሳልፈው በመስጠት በሽብርተኝነት ሥራ ተሰማርተዋል” የሚል ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
ይሁንና እነዚህ የሰላም ታጋዮች የአቶ መለስን መንግስት ያንቀጠቀጡትና ያሸበሩት ፤በሰላ ብዕራቸውና ስለነፃነት በሚሰብከው አንደበታቸው እንጂ -ድንጉጡና ሽብሩ መንግስት በፍርሀት እንደሚለው
-በሽብር ስራ በመሰማራታቸው እንዳልሆነ ተደጋግሞ መዘገቡ አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ድርጅቶች ታሪክ፤ በአሜሪካ ዓለማቀፍ የሽብርተኝነት መዝገብ ውስጥ በመስፈር፤ ህወሀት ብቸኛው ድርጅት ነው።