በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ አሜሪካን የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አዲስ ህግ አጸደቀ

ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)

የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ስጋቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ S.RES432 የተሰኘ የሰብዓዊ መብቶች ህግ በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አማካኝነት አጸደቀ።

ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓም በሜሪካን ህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አባል በሆኑት የሜሪላንድ ግዛት ሴናተር ቤንጃሚን ካርቲን አቅራቢነት በውጭ ጉድዮች ቋሚ ኮሚቴ የጸደቀው ህግ የኢትዮጵያ ህግ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ የመረመረ ሲሆን፣ የሰብዓዊ አጠባበቅ ሊሻሻል ይገባል ያላቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በህጉ እንዲካተት አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ከመጠን ያለፈ ሃይል በመጠቀም በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያ፣ አፈና እና እስር መቆም እንዳለበት፣ በኦሮሚያ የተፈጸሙ ግድያዎችን መመርመር እንዳለበት፣ ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ የተቃዋሚ አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጋዜጠኞችን መፈታት እንዳለባቸው ያስገነዝባል። አሜሪካን ለኢትዮጵያ መንግስት የምትሰጠው የሰብዓዊ እና ወታደራዊ ድጋፎች እንድትመረምር እና ቁጥጥር እንዲደረግም ያዛል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና የአሜሪካን ተራድዖ ድርጅት (USAID) አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግስት የምትሰጠውን እርዳታ ክትትል እንዲያደርጉና እንዲመረምሩ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው ያወጣው ህግ ይጠይቃል።