በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ

ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት (UNOCHA) አስታወቀ።

ድርቁ ነፍሰጡሮችንና የሚያጠቡ እናቶችንና በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳቸው እንደሆነ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ድርጅት ማክሰኞች ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በወቅታዊ የሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሪፖርትን ያወጣው ተመድ፣ በድርቁ መባባስ የተነሳ ነፍሰጡሮችና የሚያጠቡ እናቶች ከምግብ አቅርቦት ማነስ ጋር የተያያዙ ውስብስብ የጤና ችግሮች እየደረሱባቸው እንደሆነ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በአውስትራሊያና ኒውዚላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያም በኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ የሚባል ነገር የለም ሲሉ በአውስትራሊያ አገር ለሚገኝ ኤስ ቢ ኤስ ለተባለ ሬዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል። ረሃብም በኢትዮጵያ እንዳልተከሰተ ለዚሁ ሬዲዮ ጣቢያ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ትርፉ ኪዳነማሪያም በኢትዮጵያ ድርቅ ተከስቷል ቢባል እንኳን በመንግስት በቁጥጥር ስር ውሏል በማለት ተከራክረዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ በትምህርት ላይ የሚገኙ ወደ ስድስት ሚሊዮን ህጻናት ትምህርታቸውን ሊስተጓጎል እንደሚችል በቅርቡ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡና ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች የሚያስፈልገው ድጋፍ በበቂ ሁኔታ አለመገኘቱ በድርቁ አደጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያሳደረ እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት በዚሁ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፍሯል።

ድርቁን ለመከላከል ከሚያስፈልገው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሁለት ሶስተኛው ያህሉ ብቻ የተገኘ ሲሆን፣ እስከ ነሃሴ ወር ድረስ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር መገኘት እንዳለበት የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።