ህዳር 5 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በምእራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በሚገኝ አንድ ወረዳ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ 4 ወጣቶች የግንቦት 7 የእቡዕ አባላት ናቸው ተብለው በመጠርጠራቸው በደህንነት ሰዎች ተወስደው መታሰራቸውን የአማራ ክልል ወኪላችን የላከው ዘገባ ያመለክታል።
ለደህንነታቸው ሲባል የቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም የወረዳውንና ቀበሌውን ዝርዝር ከመግለጥ የተቆጠበው ዘጋቢያችን፣ ወጣቶቹ የተያዙት ኖቬምበር 7፣ 2011 ወይም ጥቅምት 30፣ 2004 ሲሆን፣ ከአንደኛው ወጣት አድርሻ በስተቀር ሶስቱ ወጣቶች ያሉበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም።
አያልሰው የተባለው ወጣት በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስሮ እንደሚገኝ ቤተሰቦቹ ማረጋጋጣቸውን የገለጠው ዘጋቢያችን ፣ ሌሎች ሶስቱ እስረኞች ግን የት እንዳተሰሩ ቤተሰቦቻቸው እንደማያውቁ ገልጧል።
በተመሳሳይ የሽብር ወንጀል የሚፈለገው ሙሉጌታ የኔአለም የተባለው ወጣት ጓደኞቹ በተያዙበት እለት በአካባቢው ባለመኖሩ ሳይያዝ መቅረቱንና አሁንም እየታደነ እንደሚገኝ ቤተሰቦቹን ዋቢ አድርጎ የላከው ዘገባ ያሳያል።
የአካባቢው ወጣቶች በመንግስት የአፈና ተግባር በእጅጉ መበሳጨታቸውን እየገለጡ ሲሆን፣ የተያዙት ወጣቶቹ
በአካባቢው ወጣቶች ዘንድ ተደማጭነት እንደነበራቸውና ወጣቶችን ለአመጽ ያነሳሳሉ በሚል ፍርሀት በደህንነት ሰዎች ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር ታውቋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከመብት እና ከዲሞክራሲ ጋር በተያያዘ ለሚነሱት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች፣ የኢትዮጵያ መንግስት ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄዎችን ለማፈን እንደሚሞክር ይታወቃል።
በቅርቡ 24 ጋዘጠኞችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች አሸባሪዎች ተብለው መታሰራቸውንና ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የመለስ መንግስት በቅርቡ ንቅናቄውንና አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አሸባሪ ብሎ መክሰሱን አውግዟል።
ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ክሱ ““የፀረ-ሽብር ህግ” ተብሎ የሚጠራው የመለስ ፓርላማ ውሳኔ በህግ፣ በህጋዊነትና በፍትህ ላይ ያደረሰውን ጥፋት አጉልቶ እንደሚያሳይና በዚህ “ህግ” ምክንያት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንዳችም የኑሮ ዋስትና የሌለው መሆኑን አሳይቷል ብለኦል።
አንዳችም ህግ በሌለበት አገር በቅድሚያ መደረግ ያለበት ነገር ህጋዊ ሥርዓትን ማቆም ነው የሚለው ግንቦት7 ፣ በመለስ መንግስት የቀረበው የሽብርተኝነት ክስ አገዛዙን የማስወገድ እንቅስቃሴ ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን የሚያመለክት ነው ብሎአል።