ሚያዚያ ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመላው ክርስቲያኖች ዘንድ ከሚከበረውን የፋሲካ በአል ጋር ተያይዞ የቅቤ እና የዶሮ ዋጋ የተጋነነ ጭማሪ ሲያሳዩ፣ በብዙ የክልል ከተሞች ደግሞ ዘይት እስከናካቴው ጠፍቷል። በአማራ ክልለ በሚገኙ ከተሞች ደግሞ፣ ከዘይት በላይ ውሃ ማግኘትም እየቸገረ ነው።
ዛሬ በአዲስአበባ ሳሪስ እና ሾላ ገበያዎችን የቃኘው ዘጋቢያችን እንደገለጸው፣ የምግብ ቅቤ የችርቻሮ ዋጋ በኪሎግራም ከ250 እስከ 300 ብር በመሸጥ ላይ ነው ። ከበአሉ በፊት የቅቤ ዋጋ በኪሎግራም ከ200 ብር የዘለለ አልነበረም ብሎአል።
የአንድ አበሻ ዶሮ ዋጋ ከ350 እስከ 400 ብር እየተጠየቀ ሲሆን፣ እምብዛም በኢትዮጵያ ባይለመድም የተዘጋጁ የአበሻ ዶሮዎች በሱፐርማርኬቶች ከብር 120 እስከ 150 በመሸጥ ላይ ናቸው።
እንዲሁም ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ20 እስከ 25፣ ነጭ ሽንኩርት ከ75 እስከ 85 ፣ ቃሪያ በኪሎ ከ30 እስከ 50 ፣ ቲማቲም በኪሎ ከ18 እስከ 20 ፣ አንድ እንቁላል ከብር 3 ከ70 እስከ 3 ከ 85 ሳንቲም በመሸጥ ላይ ነው።በሾላ የበግ ገበያ ከብር 2 ሺ እስከ 3 ሺ 500 አነስተኛና መካከለኛ በግ ማግኘት የሚቻል ሲሆን፣ ከፍ ያለ ሙክት እስከ 7 ሺ ብር ዋጋ እየተጠየቀበት ነው። ይህም ሆኖ የዛሬው የበግ ዋጋ አንጻራዊ በሆነ መልኩ መረጋጋት እንደታዬበት ዘጋቢያችን ገልጿል።
በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚታየው የዘይት እጦት ለብዙ ኢትዮጵያውያን ያልተመለሰ እንቆቅልሽ ሆኗል። ካለፉት 5 አመታት ጀምሮ ዘይት እንደልብ ማግኘት የቀረ ሲሆን፣ መንግስት የነጋዴዎችን ስራ ራሱ በመውሰድ በየቀበሌዎች ሲያከፋፍል ቆይቷል። ይሁን እንጅ መንግስት የሚያከፋፍለውን ዘይት እንደልብ ማገኘት የማይችለበት ደረጃ ላይ መደረሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። በተለይ ከአዲስ አበባ ርቀው በሚገኙ የክልል ከተሞች፣ ዘይት ብርቅዬ ሃብት ከሆነ ውሎ ያደረ ሲሆን፣ አንዳንድ ጊዜ አንድ ዘይት በወር ለማግኘት የማይችልበት ደረጃ መደረሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። የፋሲካ በአልን ተከትሎ፣ በብዙ የክልል ከተሞች ዘይት በመጥፋቱ ነዋሪዎች፣ ምሬታቸውን እየገለጹ ነው።
ከዘይት ባላነሰ መልኩ የውሃ እጥረትም በተለይ የአማራ ክልል ነዋሪዎችን እያጠቃ ነው። ባህርዳር፣ወረታ፣ቻግኒና ቡሬን የመሳሰሉ ከተሞች በውሃ ጥም እየተሰቃዩ መሆኑን የክልሉ ዘጋቢያችን ገልጿል።
ችግሩ በከፋባቸው በርካታ የአማራ ክልል ከተሞች ገዢው ፓርቲ ችግሩን እፈታለሁ በማለት በተደጋጋሚ ቃል ቢገባም እስካሁን የታየ ለውጥ የለም። ባህር ዳር ከተማ በዚህ ሳምንት ውሓ በወረፋ እንደሚከፋፈል የተገለጸ ቢሆንም፤ በተለያዩ ቀበሌዎች ከሁለት ሳምንት በላይ ውሃ ማግኘት ያልቻሉ ደንበኞች መኖራቸውን ዘጋቢያችን ጠቅሷል።
በሌላ ዜና ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው እድገት አስተማማኝ መስረት ላይ ያልቆመ በመሆኑ ኢትዮጵያ ድጋፍ ያስፈልጋታል ሲል የኖርዌይ መንግስት ጠቅሷል፤፡በኢትዮዮጵያ የተከሰተው ድርቅ አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የኖርዌይ መንግስት ለድርቅ ተጠቂዎች የሚውል ከዚህ ቀደም ከሰጠው እርዳታ በተጨማሪ ሃያ ሚሊዮን የኖርዌይ ኖሽክ ወይም ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መስጠቱን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ርሃቡ በነዋሪዎች ላይ አስከፊ ጥላውን ማጥላቱን ተከትሎ ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የእለት ከእለት የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች መሆናቸውንም ገልጿል። የርሃቡ አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰዎችን ሕይወት ከሞት ለመታደግ ይቻል ዘንድ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ሚኒስቴሩ አመልክቶ፣ በኢትዮጵያ ያለው እድገት ዘላቂነት የሌለውና አስተማማኝ መስረት ላይ ያልቆመ በመሆኑ በተለይ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል ችግሩ ተባባሶ እንደሚቀጥልና ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።
የኖርዌይ መንግስትና የኖርዌይ ግብረሰናይ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ያለውን አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ለማገዝ ቀጣይነት ያለው እርዳታ ለመስጠት ማሰባቸውን ገልጸዋል።