እነ አቶ መላኩ ፈንታ ተከላከሉ ተባሉ

ሚያዚያ ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌዴራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን በቀድሞ የጉምሩክ ኃላፊ በነበሩት አንደኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታውና ግብረ አበሮቻቸው ላይ ከተከሰሱባቸው አስራ ሰባት ክሶች በተወሰኑት የጥፋተኝነት ብይን አስተላልፎባቸዋል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ መላኩ ፈንታ የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር፣ 2ኛው ተከሳሽ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፣ 3ኛው ተከሳሽ አቶ በላቸው በየነ የኦዲት ዳይሬክተር፣ እንዲሁም አቶ ማሞ አብዲ የታክስ አማካሪ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባል እና ጸሃፊ ሆነው ስርተዋል።
አቶ መላኩ ፈንታ ሀዋስ አግሮ ቢዝነስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አቤቱታ እንዲቀየር በማድረግ 22 ሚሊየን 379 ሺህ 140 ብር ወደ መንግስት ካዝና መግባት የነበረበትን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስበ በኩላቸው ውሳኔው ተፈጻሚ እንዲሆን ትእዛዝ መስጠታቸውንና 3ኛ እና 4ኛ ተከሳሾች የቴክኒክ ኮሚቴው ውሳኔ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ክሱ አመልክቷል።
አቶ መላኩ ያማቶ ኢትዮጵያ ለተባለ ድርጅት ከ1996 እስክ 2001 ዓ.ም ድረስ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ የንግድ ስራ ገቢ ኦዲት ተደርጎ በድምሩ 48 ሚሊየን 444 ሺህ ብር ቢወሰንባቸውም፣ የግለሰቡን አቤቱታ በመቀበል እና እርሳቸው ባቋቋሙት ኮሚቴ እንዲታይ በማድረግ ወደ 34 ሚሊየን ብር ዝቅ እንዲል አድርገዋል በሚል በቀረበባቸውም ክስ ፍርድ ቤቱ ይከላከሉ ብሎአቸዋል።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ የወንጀል ችሎት የመከላከያ ምስክር ለመስማት ችሎቱ ለሰኔ 15 ቀን 2ዐዐ8 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ የአቶ መለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ በሙስና ከሰው ያሳሰሩዋቸው የመጀመሪያዎቹ ከፍተኛ ባለስልጣኖች የሆኑት በዚሁ መዝገብ የተከሰሱት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣናት ናቸው።እነ አቶ መላኩ ከታሰሩ በሁዋላ በሙስና የተዘፈቁ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት እንደሚጠየቁ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ከእነ አቶ መላኩ በሁዋላ አንድም ከፍተኛ ባለስልጣን በሙስና ተከሶ ፍርድ ቤት አልቀረበም። ኢህአዴግ ከታች ያሉ አመራሮቹን በሙስና እና በመልካም አስተዳደር ስም እየገመገመ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን ከሃላፊነት ማንሳቱን ቢገልጽም፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የሚገኙ ሹሞቹን ደፍሮ ለመንካት አልቻለም።
በአቶ መላኩ ፋንታ ላይ የቀረበውን ክስ ብዙ የአማራ ክልል ተወላጆች እና የብአዴን አባላት በጥርጣሬ ያዩታል። ግለሰቡ በክልሉ ህዝብ ላይ በተለይም ከሱዳን መሬት እና ከህወሃት የበላይነት ጋር በተያያዘ በኢህአዴግ ላይ የሚያነሱት ትችት ለእስር ዳርጓቸዋል ብለው ያስባሉ። መንግስት በኢቲቪ በሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ስለ አቶ መላኩ ያቀረበው ነገር አለመኖሩ የህዝቡን ጥርጣሬ እንዳጎላው የክልሉን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።