ህዳር 2 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ በእነ ኤልያስ ክፍሌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የከሰሳቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ፣ የፍትህ ዓምደኛ ርዮት ዓለሙ ትናንት ህዳር 1 ቀን 2004 ዓም አቀርበዋለሁ ያለው የድምጽና የምስል ማስረጃ ባለመሟላቱ ፍርድ ቤቱ ማስረጃ
የመመልከት ሂደቱ እንዲቋረጥ ወስኖ ተለዋጭ ቀጠሮ ለህዳር 6 ቀን 2004 ዓ.ም ሰጠ::
አርብ እለት ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ላይ የክሱን የሠነድ ማስረጃ ማየት ይጀምራል የተባለው ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፣ዘግይቶ 9፡05 ሰዓት ላይ የተሰዬመ ሲሆን፣ ”ዐቃቤ- ሕግ ዝግጁ ባለመሆኑ ፍርድ ቤቱ ችሎቱ የኦዲዮ ቪዲዮ ማስረጃዎችን ለማየት ስላልተመቻቸ፣ ሁኔታውን የሚያመቻቸው ባለሙያ እስካሁን ስላልመጣ፣ ባለሙያው እስኪመጣ ድረስ ሌላ ቀጠሮ ከሚቀጠር መጠበቁ የተሻለ ይሆናል‘
በማለት ችሎቱ 9፡25 ሰዓት ላይ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ችሎቱን ለመከታተል የመጡ የተከሳሽ ቤተሰቦች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾችና የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ የችሎቱን ዳግም መከፈት በትዕግስት የጠበቁ ሲሆን፣ 9 ሰአት
ከ34 ደቂቃ ላይ ቴሌቭዥን፣ የሲዲ ማጫወቻ ዴክና ሌሎች ቁሳቁሶች ወደ ችሎቱ አስገብተው ዝግጅት ማድረግ ሲጀምሩ ፣ ዳኞቹ ዳግም በመሰየማቸው 10፡25 ሰዓት ላይ የኦዲዮና የምስል ማስረጃ መቅረብ ጀመረ፡፡
ዐቃቤ- ሕጉ አቶ ብርሃኑ ወንድምአገኝ የሲዲውን ጭብጥ ለፍርድ ቤት ሲያስረዱ “አንደኛ ተከሳሽ በአሜሪካን አገር የሚኖረውን የኤሊያስ ክፍሌን አጠቃላይ የሽብር ድርጊት የሚገልጽና በተለያዩ ጊዜያት ይሄን ሥርዓት እንዴት መጣል የተናገረውን ቃለ- መጠይቁ ያስረዳልኛል” ብሏል፡፡
ለእይታ የቀረበው ሲዲ የኢሳት ቴሌቪዥን የውይይት ፕሮግራም ሲሆን ፣ በፕሮግራሙ ላይ በእንግድነት ኤሊያስ ክፍሌ እና ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በሰሜን አፍሪካና በአረቡ ዓለም ሕዝባዊ ንቅናቄ ላይ ያላቸውን የግል አስተያየትና ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሲተነትኑ ይታያል።
10፡34 ሲሆን ዐቃቤ- ሕግ ሲዲው ረጅምና ተመሳሳይ ስለሆነ በዚሁ ይቁም ብሎ ሌላ ሲዲ በማቅረብ ”ይሄ የድምጽ ሲዲ ደግሞ አራቱ ተከሳሾች ከቁጥር አንድ ተከሳሽ ኤሊያስ ክፍሌ ጋር ያላቸውን ግንኙነት
የሚያሳይ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ፍቃድ መሠረት የመረጃና የደህንነት ጽ/ቤት ባደረገው ክትትል የተጠለፈ የስልክ ልውውወጣቸው ነው‘ ብሏል፡፡
የመሐል ዳኛው የድምጽ ማስረጃው ወደ ጽሑፍ የተገለበጠ ስላለው እዚህ ካለ እርሱ ቢቀርብ የሚል አማራጭ ያቀረቡ ሲሆን፣ ዐቃቤ- ሕግ እኛ ድምጻቸው እንዲቀርብ ነው እንጂ ወደ ጽሑፍ የተቀየረው
110 ገጽ አለን ሲል መልሷል፡፡
የርዮት ጠበቃ ሞላ ዘገየ “ደንበኛዬ የተከሰሰችው በግብረአበርነት ነው፣ ክሱ የሚለው ግን በዋና ወንጀል አድራጊነትና በተባባሪነት ነው፤ ስለዚህ መጀመሪያ የሰማነው ቪዲዮ መቆረጥ የለበትም፤ ለፍትህ አሰጣጥ ሲባል ዐቃቤ- ሕግ የሚፈልገው ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም የሚጠቅመውን ሁሉ ፍርድ ቤቱ በትክክል ማየት አለበት በማለት ተቃውሟቸውን” አሰምተዋል፡፡
ዐቃቤ-ሕግ “ኤሊያስ ክፍሌ ይሄን መንግሥት ለመጣል ብዙ ቃለ- መጠይቆች ሰጥቷል፣ እነዚህ ጠበቆች የቆሙት ደግሞ ለኤሊያስ ክፍሌ ሳይሆን እዚህ ላሉት ተከሳሾች ነውና ስለእርሱ አይመለከታቸውም፤ በዚህ ላይ ሁለተኛው የድምጽ ማስረጃ ላይ በደህንነትና መረጃ ክፍል በጠለፋ የተያዘ ማስረጃ አለ፣ ስለዚህ ስለኤሊያስ ያቀረቡትን ውድቅ ይደረግልኝ” በማለት አቤቱታ አቅርቧል፡፡
የመሐል ዳኛው ከግራ ቀኝ ዳኞች ጋር ከተወያዩ በኋላ “ክሱ የቀረበው በጋራ በመሆኑ፣ አንደኛው ተከሳሽ ኤሊያስ ክፍሌን የሚመለከቱት ቀርበው ፣ያልተከሰሱት ሲሳይ አጌናን የሚመለከተው ግን እንዳይቀርብ ወስነናል” ብለዋል፡፡
በዚህ ውሳኔ መሠረት ተቋርጦ የነበረው ሲዲ መታየት ቢጀምርም ተከታታይ ክፍሉን ዐቃቤ- ሕግ ለማቅረብ ባለመቻሉ ፣ የመሐል ዳኛው “ዐቃቤ- ሕግ ማስረጃው የሚታይበትን ሁኔታ ያመቻቻችሁ አትመስሉም” በማለት ከተቹ በኋላ የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን ለማየት ለህዳር 6 ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱ ተበትኖአል እስካሁን በተከሳሾች ላይ የቀረቡት ማስረጃ በመሉ አስቂኝ ናቸው ሲሉ አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ጠበቃ ለኢሳት ተናግረዋል።
በእነ ርእዮት አለሙ ላይ ማስረጃ በመጥፋቱ አቃቤ ህግ የሚይዘውና የሚጨብጠው ማጣቱን በችሎቱ የተሳተፉት ታዳሚዎች ለዘጋቢያችን ተናግረዋል። በእስር ላይ በሚገኙት የስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የቀረበው
የተቀነባበረ የፊልም ማስረጃ የመለስንም መንግስት የፍትህ ግንዛቤ ያጋለጠ መሆኑን የስዊድን ጋዜጦች መዘገባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
አቶ መለስ በቅርቡ በፓርላማ ፊት ቀርበው ተጨባጭ፣ በቂና ጠንካራ ማስረጃ አለን ብለው መናገራቸው ይታወሳል።