የአቶ መለስ መንግስት በስድስት ጋዜጠኞች ላይ የመረሰተውን የሽብርተኝነት ክስ በፍጥነት እንዲያነሳ ሲ.ፒ.ጄ ጠየቀ

ህዳር 2 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የአቶ መለስ መንግስት በስድስት ጋዜጠኞች ላይ የመረሰተውን የሽብርተኝነት ክስ በፍጥነት እንዲያነሳ፤ መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገው ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት-ሲ.ፒ.ጄ ጠየቀ።

ሲ.ፒ.ጄ   ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ባወጣው የፀረ-ሽብር ህግ መሰረት ሰሞኑን ስድስት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በ 24 ሰዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መመስረቱን በመጥቀስ፤  ክስ ከተመሰረተባቸው ጋዜጠኞች መካከል እስክንድር ነጋ  ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ   በእስር ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።

በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው አምስቱ ጋዜጠኞች ደግሞ፦የአዲስ ቮይስ ድረ-ገፅ አዘጋጅ  ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ የአዲስ ድምፅ ሬዲዮ አዘጋጅ ጋዜጠኛ አበበ በለው፣ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን አዘጋጅ ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም  እና የአዲስ ነገር ድረ ገጽ አዘጋጆች   የሆኑት ጋዜጠኛ አቢይ ተክለማርያምና ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ ናቸው።

አዲሱ የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብርተኝነት ህግ፤ ጋዜጠኞች-  በመንግስት “ሽብርተኛ”ስለተባሉ ድርጅቶች እንቅስቃሴ ምንም ነገር እንዳይፅፉ  የሚገድብ መሆኑን ያወሳው ሲ.ፒ.ጄ፤ ጋዜጠኞቹ የተከሰሱት  መንግስት በዚህ ዓመት ፦”ሽብርተኛ”ብሎ የፈረጀውን ተቃዋሚ ፓርቲ ፤ማለትም ግንቦት ሰባትን  ረድታችሁዋል ተብለው እንደሆነ ገልጿል።

የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል፤ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፦”ጋዜጠኞቹ ለግንቦት ሰባት ድጋፍና ልገሳ አድርገዋል”ብለዋል።

የኢትዮጵያን መንግስት ለመጣል ሌት ተቀን እየሰራ ነው ያሉትን የኤርትራን መንግስት የከሰሱት አቶ ሽመልስ፤ጋዜጠኞቹ ከኤርትራ መንግስት የጦር መሳሪያ እንደተቀበሉና ኢትዮጵያ ውስጥ በማፈንዳት የሽብርተኝ  ተግባር ለመፈፀም እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የሲ.ፒ.ጄ የምሥራቅ አፍሪቃ ዳይሬክተር ቶም ሩድስ ግን፤የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መንግስትን በሚተቹ ጋዜጠኞች ላይ የተመሰረተውን የሽብርተኝነት ክስ፦ “ያልተረጋገጠና  አስቂኝ “ነው ያሉት።

መንግስት ክሱን የሚያረጋግጥ አንድም ተጨበጭ መረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ የጠቆሙት ዳይሬክተር ቶም ሩድስ፤ የስድስቱንም ጋዜጠኞች ክስ በቶሎ አንዲያነሳ አሣስበዋል።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ፋሲል የኔዓለም ምርጫ 97 ትን ተከትሎ ከቅንጅት አመራሮች ጋር ታስረው እንደነበር ያስታወሰው ሲ.ፒ.ጄ፤ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽና አብይ ተክለማርያም ደግሞ፤  በ2009 ዓመተ ምህረት የሽብርተኝነት ክስ ሊመሰረትባቸው እንደሆነ በደረሳቸው መረጃ መሰረት “አዲስ ነገር” የተሰኘውን ጋዜጣቸውን ዘግተው ለስደት መዳረጋቸውን አውስቷል።

እንዲሁም፤ጋዜጠኛ አበበ ገላው በ1999 አገሩን ለቅቆ መውጣቱንና አበበ በለው ደግሞ  ከዋሽንግተን የሚሰራጭ ራዲዮ መጀመሩንና  መንግስትን የሚተቹ ይዘት ያላቸው ፕሮጋራሞች በሬዲዮው
እንደሚሰራጩ ሲ.ፒ.ጄ አመልክቷል።

ኢትዮጵያ  ጋዜጠኞችን ለስደት በመዳረግ ከዓለም የመጀመሪያዋ አገር እንደሆነችም፤ ሲ.ፒ.ጄ በመግለጫው አስታውሷል