ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)
በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የወጣቶች ክንፍን በማደራጀት ከመንግስት ጋር ውጊያን ሊያካሄዱ ነበር የተባሉ 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተዘገበ።
ተጠርጣሪዎቹ በተለምዶ ቦሌ ቡልቡላ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት የእምነት ስነስርዓት የሚያካሄዱ በመምሰል ለወጣቶች ክንፍ አባላት ሲመለምሉና ሲያደራጁ መቆየታቸውን ከሳሽ አቃቤ ህግ በክሱ አቅርቧል ሲል ሪፖርተር ገልጿል።
ተጠርጣሪዎቹ መንግስት የኦሮሞን መሬት እየቆራረሰ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ እጅና ጓንት በመሆን መንግስትን መዋጋት አለበት የሚል ቅስቀሳን ሲያካሄዱ መቆየታቸውንም በጠርጣሪዎቹ ላይ የቀረበን ክስ ዋቢ በማድረግ በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሃብቷሙ ሚልከሳ ጫሊ ኦና ረዳት ሳጅን ጫላ ፍቃዱ አብደታ የተባሉ ግለሰቦች የወጣቶቹ ክንፍ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በመሆን እንቅስቃሴ ማካሄዳቸውንም አቃቤ ህግ በክሱ አመልክቷል።
በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪዎቹ በአንድ ግቢ ውስጥ 60 የሚሆኑ አባላትን በማሰባሰብና የኦነግን ባንዲራ እንዲይዙ በማድረግ ለድርጅቱ ለጊዜው መጠኑ ያልታወቀ ገቢ ማሰባሰባቸውንም ከሳሽ አቃቢ ህግ ባቀረበው የሽብርተኛ ክስ አስፍሯል።
ባለፈው ህዳር ወር በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎች ላይ የቀረበውን ክስ በመመልከት ፍርድ ቤቱ ለሚያዚያ 7 ፥ 2008 አም ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከአራት ወራት በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ቢገለጽም፣ እስካሁን ድረስ ለምን ክስ እንዳልተመሰረተባቸው የታወቀ ነገር የሌለ ሲሆን፣ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የኦነግ አባላት ናችሁ ተብለው ለእስር መዳረጋቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በቁጥጥር ስር ዉሏል ቢሉም ተቃውሞው አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።