ብሪታኒይ ለኢትዮጵያ በምትሰጠው ድጋፍ ላይ ተቃውሞ መጀመሩን የዜና አውታሮች እየዘገቡ ነው

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)

የብሪታንያ መንግስት ለኢትዮጵያ በሚሰጠው የደህንነትና የጸጥታ ድጋፍ ዙሪያ አዲስ ተቃውሞ መቅረብ መጀመሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።

ሃገሪቱ ዜጋዋን አስሮ ለሚገኝ ሃገር በአየመቱ ወደ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ አካባቢ በመመደብ የጸጥታ ሃይሎች ልዩ ስልጠናን እንዲያገኙ ማድረጓ የብሪታኒያ የተለያዩ አካላት በመቃወም ላይ መሆናቸውን ዴይሊ ሜይል የተሰኘ ጋዜጣ በሳምንቱ መገባደጃ ባወጣው ሪፖርት አስነብቧል።

የብሪታኒያ መንግስት አጋር አድርጎ ድጋፍ ከሚሰጣቸው ሃገራት መካከል የሰላ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ትችት የሚቀርብባቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጎረቤት ጂቡቲና ሩዋንዳ የሚገኙበት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም 35 የሚደርሱ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ልዩ የስለላ ስልጠና እያገኙ እንደሆነ ታውቋል።

ይሁንና፣ ሃገሪቱ ከእነዚሁ ሃገራት እየሰጠችው ያለው ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ አምባገነን ሃገሮች የሚደግፍ ነው በማለት ትችት እየቀረበ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።

የብሪታኒያ የታክስ ከፋዮች ገንዘብ የሃገሪቱን ዜጋ አስሮ ከሚገኝ ሃገር በመዋል ላይ መሆኑ እጅግ አሳዛኝና የሚያስደነግጥ ዜና ነው ሲል የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነው ሪፕሪቭ ገልጿል።

የብሪታኒያ መንግስት ለኢትዮጵያ እየሰጠ ያለው የጸጥታና የደህንነት ድጋፍ በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት በሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

የሃገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለ የደህንነትና የጸጥታ ትብብር በጉብኝቱ ወቅት ሰፊ ምክክር እንደሚካሄድበት አስታውቀዋል።

የብሪታኒያ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ከእስር ለማስለቀቅ ቸልተኛ ሆነዋል በማለት በዚህ በአሜሪካ በተለያዩ የአለማችን ሃገራት የተቃውሞ ሰልፎች ሲካሄዱ መቆየታቸውም ይታወሳል።