የአጣዳፊ ተቅማት በሽታ በኦሮሚያ፣ ደቡብና ሶማሊ ክልሎች እየተዛመተ ነው

ኢሳት (መጋቢት 23 ፥ 2008)

በቅርቡ በሶማሊና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው የአጣዳፊ ተቅማት በሽታ ወደሌሎች አጎራባች ስፍራዎች በመዛመት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ።

በኦሮሚያ ሞያሌ ወረዳ ተከስቶ የነበረው ይኸው በሽታ፣ ገላና እና አባያ ወደተባሉ ወረዳዎች የተዛመተ ሲሆን፣ በሶማሊ ክልል በሚገኘው የሃደት ወረዳም የአጣዳፊ ተቅማት በሽታው እየተዛመተ መሆኑ ታውቋል።

በደቡብ ክልል ደግሞ የአማሮ ወረዳና የአርባምንጭ ከተማ አካባቢዎች ሰዎችን ለአጣዳፊ ህልፈት የሚዳርገው ተላላፊ በሽታ መዛመቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።

በበሽታው ስለተያዙ ሰዎች ቁጥር ዝርዝር መረጃን ያላቀረበው ድርጅቱ፣ በበሽታው ከአራት ወር ጀምሮ መከሰቱንና እስካሁን ድረስም እልባት አለማግኘቱን ባወጣው ሪፖርት ገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በቅርቡ ከ100 የሚበልጡ ሰዎች በበሽታው ተይዘው አርባ ምንጭ ሆስፒታል መግባታቸው ማስታወቁ ይታወሳል።

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለውሃ እጥረት ለተላላፊ በሽታው መቀስቀስና መዛመት ምክንያት መሆኑን የጤና ባለሙያዎች የገለፁ ሲሆን በበሽታው የተያዙ ሰዎችም አፋጣኝ ህክምና ካላገኙ በቶሎ ሊሞቱ እንደሚችሉ አሳስበዋል።