በድርቅ የተጠቁ 106 ወረዳዎች ልዩ ክትትል ይፈልጋሉ ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 23 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለውን የድርቅ አደጋ መባባስ ተከትሎ 186 ወረዳዎች ልዩ ክትትልን የሚፈልጉ ሆነው መፈረጃቸውን የተባባሩት መንግስታት ድርጅት አርብ ዕለት አስታወቀ።

በሶማሊ፣ አፋር፣ ትግራይና አማራ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች አሳሳቢ የሆነ የምግብ እጥረት ከፍተኛ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝም ታውቋል።

የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው እርዳታ በወቅቱ እየደረሰ አለመሆኑ ችግሩን እንዳሳሰበው ገልጿል።

በዚሁ የሃገሪቱ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ሪፖርቱን ያቀረበው የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በአንደኛ ደረጃ ከተፈረጁት 186 ወረዳዎች መካከል በ61 ውስጥ ድጋፍን የሚያደርጉ ተቋማት እንደሌሉም ይፋ አድርጓል።

በሶማሊ ክልል የሚገኙት የቀላፎና የደምባል ወረዳዎች፣ በትግራይ ክልል የታንኳ አበርገል፣ በአፋር ክልል የአደር እና የአባል ወረዳዎች እንዲሁም በአማራ ክልል የደሴ ዙሪያ ወረዳዎች አሳሳቢ የሆነ የምግብ እጥረት ጉዳት እያደረሰባቸው እንደሚገኝ ታዉቋል።

በአካባቢው ተከስቶ ያለውን ይህንኑ አደጋ ለመከላከል አፋጣኝ ርብርብ መደረግ እንዳለበት የህጻናት መርጃ ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በበኩላቸው ወደሃገሪቱ መግባት ያለበት የእርዳታ አቅርቦት በታሰበው መጠንና ወቅት ባለመድረሱ ሳቢያ ድርቁ ከተጠበቀው በላይ ጉዳትን እያደረሰ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

በጅቡቲ ወደብ የእርዳታ እህልን የጫኑ አስር መርከቦች በወደቡ መጨናነቅ ምክንያት የእርዳታ እህላቸውን ሳያወርዱ (ሳያራግፉ) እየተጠባበቁ እንደሚገኝ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሰሞኑን መዘገባቸው ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው የእርዳታ እህሉ ቅድሚያ እንዲሰጠው እየተደረገ ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥተዋል።

የእርዳታ እህልን ከሚጠባበቁ ሰዎች መካከል ስድስት ሚሊዮን ህጻናት ሲሆኑ የተረጂዎች ቁጥር 10.2 ሚሊዮን መሆኑም ይታወቃል።