ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዝርዝሩን የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን እንደገለፀው ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘው በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ይቀርባሉ ተብሎ ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው የአንድነት ፓርቲ ም/ል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌ፣ የፓርቲው የአመራር አባላት ናትናኤል መኮንን፣ አሳምነው ብርሃኑ፣ የመኢዴፓ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ እና ታዋቂው ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ እስክንድር ነጋ በሰአቱና በቦታው አልተገኙም።
ቤተሰቦቻቸው፣ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባላት የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አስራት ጣሴ፣ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እስከ ቀኑ 9፡00 ሰዓት በቦታው ተገኝተው ይጠባበቃሉ።
በስልክ በተገኘ አንድ መረጃ እስረኞቹ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ሊያቀርቧቸው ነው በመባሉ ሁሉም ሰው ወደ መኪና ያለው በመኪና የሌለው በታክሲ እየተሳፈረ ነጎደ።
9፡00 አካባቢ ልደታ ፍርድ ቤት ስንደርስ ፖሊስ እሥረኛችን በአቡቶቡስ ውስጥ ከነፍራሻቸውና ጓዛቸው ጭኖ ማንኛውንም ሰው አላስጠጋ ብሎ ጥበቃ ያደርግ ነበር። የእስክንድር ነጋ ባለቤት የሆነችው ጋዜጠኛ ሠርካለም ፋሲልና የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶም ወደ አካባቢው እንዳይጠጉ ፖሊሶች በቁጣ አባረሩዋቸው፡፡
10፡00 ሰዓት ላይ እስረኞቹ ሶስተኛ ወንጀል ችሎት ሲገቡ በርካታ አዳዲስ ተከሳሾች ከእነርሱ ክስ ጋር አብረው የተካተቱ ሲሆን አቶ ዘመኑ ሞላ እና አሳምነው ብርሃኑን ግን አልተገኙም፡፡
የመሐል ዳኛው ለተከሳሾች ” ዛሬ የቀረባችሁት ዐቃቤ- ሕግ ክስ ስለሚያቀርብባችሁ ነው አሉ፡፡ ከዚያም ዐቃቤ- ሕጉ 17 ገጽ ያለው የክስ ቻርጅ ለሁሉም አንድ ዓይነት እና በትልቁ ኤንቨሎፕ ማስረጃ ያላቸውን ዶክመንቶች አባሪ አድርጎ አሸከማቸው፡፡
ሁሉም እስረኛች እጅግ ተጎሳቁለዋል፤ ገላቸውን ታጥበው የሚያውቁ አይመስልም፤ ሁሉም የከሱና የጠቆሩ ቢሆንም የእስክንድር ነጋ እና የናትናኤል መኮንን ሁኔታ ግን እጅግ ያሳዝናል፤ አንዷለም አራጌ ምንም ለመናገር ፈቃደኛ አይመስልም ብቻ የትዝብትና የምጸት ፈገግታ ያሳያል፡፡
የግራ ዳኛው “ሁላችሁም የተከሰሳችሁበት ክስ የዋስትና መብት የሚያሰጣችሁ አይደለም፤ ነገር ግን ጠበቃ የማቆም መብት ስላላችሁ ጠበቃ ማቆም ትችላላችሁ፣ አቅማችን ጠበቃ ለመቅጠር አይፈቅድም የምትሉ ካላችሁ ደግሞ ተናገሩና ቃለ መሐላ ፈጽማችሁ መንግስት ጠበቃ ሊያቆምላችሁ ይችላል” አሉ፡፡
የመሐል ዳኛው አያያዙና ” የክሱን ቻርጁን በደንብ ተመልከቱት፤ ዛሬ ጊዜ አይበቃችሁም ጊዜ ተሰጥቷችሁ በቀጣይ ቀጠሮ የክሱ ክርክር ይጀመራል፣ ዛሬ ፍርድ ቤቱ ክሱ የሚቆምበትን ቀን ይወስናል” አሉ፡፡
በዚህ መሐል እጅግ የተጎሳቆለው 2ተኛው ተከሳሽ ናትናኤል መኮንን “ለፍርድ ቤቱ የምናገረው አለኝ እጅግ የከፋ በደል ተፈጽሞብኛል” ሲል ብሶቱን ገለጸ፡፡ ዳኛውም ፡- “ዛሬ ፍርድ ቤቱ ክሱን መስማት አልጀመረም ለዚህ ቀነ ቀጠሮ ይሰጣል” አሉ
ናትናኤልም መልሶ” እባካችሁ በደል ስለተፈጸመብኝ ልናገር”፡ አለ ደግሞ ዳኛውም ፡- “ክሱ ሲሰማ ነው ማቅረብ የምትችለው፣ አሁን እያደረግን ያለነው ክሱን አይታችሁ የምትቀርቡበትን ቀን ልንወስን ነው እና ጠበቃ ማቆም የማትችሉትን መንግሥት ጠበቃ ያቁምላችሁዋል አሉ
በዚህ መሐል ተከሳሽ ቁጥር 3፣4፣5 እና 6 ጠበቃ መቅጠር እንደማይችሉ ገልጸው ቃለ መሐላ ፈጸሙ፡፡ የዐቃቤ- ሕግ 5ተኛ ተከሳሽም “ላለፉት 2 ወር ማዕከላዊ እስር ቤት ሆን ብለው ከቤተሰቦቼ ጋር እንዳልገናኝ አድርገውኛል፡፡ የአራዳ ጽ/ ቤት መብቴ እንዲከበር ትዕዛዝ ቢሰጥልኝም አልተከበረም፡፡ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ውስጥ ሕገ-መንግሥቱ አይከበርም፣ ራዲዮ፣ ጋዜጣ፣ መጽሐፍ እንዲገባልኝ አራዳ ምድብ ችሎት ቢፈቅድልኝም እነርሱ አይተገብሩትም” ብሏል፡፡
2ኛው ተከሳሽ ናትናኤል መኮንን እባካችሁኝ ስሙኝ እያለ ደጋግሞ በመማጸኑ ፍርድ ቤቱ እሺ ተናገር ብሎ ማድመጥ ጀመረ፡፡ ናትናኤልም ቀጠለ ”እኔ በዚህ በተባለው ወንጀል ተጠርጥሬ በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ እገኛለሁ፡፡ ከ3 እስከ 26 ባሉት ፣ ለ23 ቀናት የፌዴራል ማዕከላዊ ፖሊስ አዛዥና በሥሮቻቸው ያሉት መርማሪዎች የአካል፣ የሞራል እና የስብዕና በደልና ጥቃቶችን ፈጽመውብኛል፡፡ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡ ደብድበውኛል፡፡ እንባና ሲቃይ እየተናነቀው ቀጠለ ። በነዚህ ቀናት ልብሴን አስወልቀው እርቃኔን ውሃ እየደፉብኝ ይሄ ነው የተባለ ምግብ ለ7 ቀናት እንዳይደርሰኝ አድርገው ፣ የቤተሰቦቼን ምግብ በርቀት እያሳዩኝ፣ ቤተሰቦቼን ምግቡ እየደረሰኝ አይደለም አታምጡ እንኳ እንዳልል እድል አጥቼ በማለት ሲናገር እንደገና ሲቃ ያዘው እንባው አላናግር አለው። እንደምንም እምባውን ተቆጣጥሮ “ለ23 ቀናት እጄ ወደ ኋላ ታሥሮ፣ ለ2 ቀን እነርሱ እንድልላቸው የሚፈልጉትን ካልተናገርኩ እንደማይለቁኝ ዝተውብኛል። ይሄን ሁሉ ለአራዳ ምድብ ችሎት ከዚህ ቀደም ተናግሬ ዛሬ ውሳኔ ሊሰጠኝና እነርሱም ቀርበው ቃል እንዲሰጡ በታዘዘበት ወቅት ነው እንደ አዲስ ወደዚህ የመጣነው፡፡
ይሄም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ኮሚሽነር ሊጎበኙን በመጡበት ወቅት እኔ ያለሁበትን ብሎክ ሳይመለከቱ ፊት ለፊቱን ብቻ አይተው ሄደው ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት የለም ብለው መግለጫ በመስጠት በበደሌ ላይ ክህደት ፈጽመውብኛል፡፡ ይህ ተቋም በእኔ ላይ የፈጸመብኝ በደል በማለት ሊቀጥል ሲል ዳኛው አቋረጡትና ” ይሄ አሁን የምተታወራው ከክርክሩ አግባብ ጋር ተገቢ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በክርክሩ መቅረብ ሲጀምር ያቅርቡትና ያኔ ተመልክተን ብይን እየተሰጠበት ይሄዳል፡፡ የሚቀርብበት አግባብ ስላለው ያኔ ቢቀርብ መልካም ነው፡፡ አሁን ያደመጥንዎት አንዴ መናገር ስለጀመሩ ነው፡፡” አሉ።
ዳኞች ትንሽ ከተነጋገሩ በኋላ አሁን ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ያምሩ፡፡ ዐቃቤ- ሕግ በሌሉበት የሚታዩ ሰዎችን በጋዜጣ ጥሪ አድርግ፡፡ለህዳር 5 ብይን ልንሰጥ ነው አሉ። ዐቃቤ- ህጉም ” 35 የሚሆኑ የሰው ምስክሮች እሉኝ፣ ለተከሳሾች በሰጠሁት የክስ ቻርጅ ላይ የምስክሮችን ሥም ዝርዝር ያላካተትኩት ለደህንነታቸው ሲባል ነው፡፡ ለፍርድ ቤቱ ያቀረብኩት ላይ ግን ተካተዋል፡፡ የኦዲዮ ማስረጃዎችም አለኝ፡፡” አለ።
ፍርድ ቤቱ ” ከ3 እስከ 6 ተራ ቁጥር ያሉት ተከሳሾች ጠበቃ በመንግሥት እንዲቆምላቸው እንዲደረግ ታዟል፤ ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብታቸውን የሚያሳጣ በመሆኑ ወደ አዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ያምሩ ሲል ወስኖ” ችሎቱ ተበትኖአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፤ በስዊድን ጋዜጠኞች ላይ የታየው የቪዲዮ ማስረጃ አቃቢ ህግ አቀነባብሮ ማቅረቡ ተጋለጠ አቃቢ ህግ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬና ጆሀን ፒርሰን መሳሪያ ታጥቀውና ስለጠና ወስደው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ለማስረዳት ያቀረበው የፊዲዮ ማስረጃ የጥይት ተኩስ ድምጽ ከጀርባው ገብቶበታል።
ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በቀረበው የቪዲዮ ማስረጃ ላይ የተኩስ ድምጽ አልነበረም አሁን በማጠቃለያው ላይ የተኩስ ድምጽ እንዴት ሊገባ ቻለ ብለው ሲጠይቁት፣ አቃቢ ህጉም አዎ ፊልሙን ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ አቀነባብረነዋል በማለት ለማመን ተገዶአል።
የስዊድን የመገናኛ ብዙሀን በኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት ላይ የሚያላግጡ ዘገባዎችን እያቀረቡ ነው። የኢትዮጵያ የፍትህ ስርአት በዚህ ደረጃ የዘቀጠ ነው ብለው አለማሰባቸውን አስተያየት ሰጪዎች በጋዜጦች ላይ አስፍረዋል።
በጋዜጠኞችና በፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ላይ የሚቀርበውም የፈጠራ ክስ በተመሳሳይ የተቀነባበረ መረጃ ላይ ተመስርቶ መሆኑ፣ የመለስ መንግስት የፍትህ ስርአቱን ለፖለቲካ ስልጣን እድሜው ማራዘሚያ እንዳዋለው አስተያየቶች ተሰጥተዋል።