የኢህአዴግ መንግሥት ሽብርተኞች ብሎ በአንደኛ ተከሳሽ ኤልያስ ክፍሌ የክስ ፋይል በከሰሳቸው ላይ ዐቃቤ- ሕግ የሰው ምሥክሮችን አሰማ

ጥቅምት 30 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢህአዴግ መንግሥት ሽብርተኞች ብሎ በአንደኛ ተከሳሽ ኤልያስ ክፍሌ የክስ ፋይል የከሰሳቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢብዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ዘሪሁን ገብረእግዚያብሄር፣ የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬ፣ ሂሩት ክፍሌ እና የፍትህ ጋዜጣ ዓምደኛ ርእዮት ዓለሙ ላይ ዐቃቤ- ሕግ የሰው ምሥክሮችን አሰማ፤ የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን ደግሞ ለማቅረብ ለዓርብ ህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ምስክር አድርጎ ያመጣቸው አብዛኞቹ በአሥራ ቤት ዕድሜ የሚገኙ እና ራሳቸውን በኑሮ መደጎም ያቃታቸው የአብቶቡስ ተራ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የተደራጁ ሊስትሮች እና ሶፍት ወረቀት ሻጮች መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ሲገልጹ ተስተውሏል፡፡

ዐቃቤ- ሕግ ለፍርድ ቤቱ የክሱን ጭብጥ ሲያስረዳ  አንደኛው ምስክሬ በሁለተኛው ተከሳሽ ላይ የሚያስረዱት በአዲስ አበባ በለሊት ገንዘብ እየተከፈላቸው ”መለስ በቃ‘ እያሉ በመርካቶ- አዳራሽ፣ ሀብተጊዮርጊስ፣ ተክለሃይማኖት፣ ጥቁር አንበሳ አካባቢ ሲያስጽፉና ገንዘብ ሲከፍሉ እንደነበር፣ ሦስተኛ ተከሳሽ ውብሸት ታዬ የተለጠፉትን ቦታዎች ፎቶግራፍ ሲያነሳ እንደነበር ይመሰክራሉ ብሎአል።

የመጀመሪያ ምስክር አብርሃም ተሰማ የተባለ በአቡቶቡስ ተራ አካባቢ አልጋ ተከራይ መሆኑን እና ቋሚ አድራሻ እንደሌለው ገልፆ “ከግንቦት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ቦና ታከለ በሚባል የአውቶቡስ ተራ ሊስትሮ ጠያቂነት ለሊት- ለሊት 70 ብር እየተከፈለው በቀይ ቀለምና በቡርሽ በቃ የሚል ጽሑፍ በአቡቶቡስ ተራ- አዳራሽ ፣ ሀብተጊዮርጊስ፣ ጊዮርጊስ የባስ ፌርማታ፣ ተክለሃይማኖትና ጥቁር አንበሳ አካባቢ እንደፃፈ ተናግሮ በሦስተኛው ቀን ግን መስቀል አደባባይ የመለስ ፎቶ ላይ ”መለስ በቃህ‘ ብሎ ለመጻፍ ከጓደኛው ጋር ሄዶ በወቅቱ ፖሊሶች ስለነበሩ ትቶ መመለሱን፤ ወደ ክልሎችም በመሄድ ለመፃፍ እቅድ እንደነበረው ገልጧል፡፡

ሁለተኛው የዓቃቤ- ሕግ ምስክር ጉችዬ ላቀው በአብቶቡስ ተራ አካባቢ ጎዳና ተዳዳሪ መሆኑን ገልፆ ቦና ታከለ የሚባል በጫማ መጥረግ  የሚተዳደር ልጅ የግርግዳ ጽሑፍ እንፃፍ እንዳለውና ከአብርሃም ጋር በመሆን ከምሽቱ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በአቶ ዘሪሁን በተነገራቸው ቦታ እየተዘዋወሩ እንደፃፉ ተናግሯል፡፡

የዐቃቤ- ሕግ ሦስተኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው ቦና ታከለ ሲሆን ዕድሜው 20 መሆኑን፣ ሥራው ሊስትሮ እንደሆነና ሰላሳ ሁለት ቀበሌ አልጋ ተከራይቶ እንደሚኖር ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ ፣ ” አቶ ዘሪሁን ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ጫማ ያስጠርገኝ ስለነበር አውቀው ነበር፣  የአንድነት ፓርቲን መታወቂያ ስጠኝ ብዬው መቶ አምሳ ብር ያስከፍላል ብሎ ነግሮኝ ሃያ- ሃያ ብር አጠራቅሜ ሰጠሁትና የአባልነት  መታወቂያ ሰጠኝ፣ ከዚያ  በጣም ተግባባን ፣ ውብሸትን ግን አንድ ግዜ ብቻ ነው ከአቶ ዘሪሁን ጋር ያየሁት፡፡” ብሎአል

“አንድ ቀን አቶ ዘሪሁን  350 ብር እከፍልሃለው መለስ በቃ እያልክ በየቦታው ፃፍ አለኝ  እኔም  አብርሃምን 130 ብር እሰጥሃለሁ ፃፍ አልኩት እና በመጀመሪያው ለሊት አብቶቡስ ተራ- አዳራሽ ፃፍን ፣ በበነጋታው ዘሪሁን መጥቶ አይቶ ከፈለኝ፣ በሚቀጥለው ቀን መስቀል አደባባይ ሂድና የመለስ ፎቶ ሥር በቃህ ብለህ ፃፍ 1100 ብር እከፍልሃለሁ አለኝና ተስማምተን ከምሽቱ ለሊት ከአብርሃም ጋር ሄደን ፖሊሶችን አይተን ሳንጽፍ ተመለስን፣
በቀጣዩ ቀን ግን ጊዮርጊስ፣ ተክለሃይማኖትና ጥቁር አንበሳ አካባቢ ፃፍን ብሏል፡፡

ሂሳብ በምንቀባበልበት ወቅትም አብቶቡስ ተራ አካባቢ ፎርቹን ካፌ ውስጥ ውብሸት ድንገት መጣና ዘሪሁን ሄዶ ፎቶ እናንሳ ብሎ ሲያዘው ውብሸት ደግሞ አንስቼዋለሁ ሲለው ሰምቻለው፡፡ ያኔ ዘሪሁን ለእኛ በድምሩ 5 መቶ ብር ከፈለን ፣ በቅርቡም የመጓጓዠ ብር እሰጥህና አምቦ፣ ሻሸመኔ እና ጋምቤላ ሄደህ በቃ እያልክ ትጽፋለህ ብሎኝ ተስማማን ብሏል፡፡

የተከሳሽ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ባነሱት መስቀለኛ ጥያቄ ላይ ” ውብሸትን የማውቀው አንድ ጊዜ ብቻ  ነው ብለሃል ፣ ስሙን እንዴት አወቅክ?’ ሲሉት በምርመራ ላይ ፖሊስ ነው የነገረኝ አለ፡፡

4ተኛ የዐቃቤ- ህግ ምስክር ሂደቱ ከተጀመረ በኋላ በመምጣቱ ለብቻው ቃለ መሐላ እንዲፈጽም የተደረገ ሲሆን.  ዐቃቤ- ሕግ ምስክሩ 4ተኛ ተከሳሽ ሂሩት ክፍሌ የበቃ ቡድን የአዲስ አበባ ተወካይ እንደነበረችና በአሜሪካን አገር ከሚኖረው ኤሊያስ ክፍሌ ጋር እንደምትገናኝ ምስክሩ የተለያዩ ሥራዎች እንዲሰራ ክፍያ የፈጸመችና የተዋዋለች እንደነበር ይመሰክርልኛል ሲል ለችሎት አቅርቦታል፡፡

ጌታሁን ዮሐንስ የተባለው የዐቃቤ- ሕግ ምስክር በሥሙ የሚጠራ በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኝ የተሸከርካሪ ጋራጅ እንዳለውና ሂሩትን የሚያውቃት ቀኑን በማያስታውሰው ሚያዚያ 2003 ዓ.ም መኪና ልታሰራው መጥታ እንደሆነ ገልፆ ፣ ” ቀደም ሲል ግን በሌላ ወንጀል በማረሚያ ቤት በታሰርበት ወቅት እርሷን ከግንቦት 7 ፓርቲ ታሳሪዎች ጋር አይቻት በዓይን አውቃት ነበር ፣ አንድ ቀን ጋራጄ መኪና ልታሰራኝ መጥታ በቃ ብዬ በሀዋሳ አደባባይ  እንድጽፍና  በደቡቡ ክልል የሚጽፉ ልጆችን እንዳስተባብርና ጠየቀችኝ፡፡ ለቀለም መግዣም ብላ 2 ሺህ ብር ከፍላኛለች እና ሥሙን ካሌብ ካለኝና በኋላ ኤልያስ ክፍሌ ከአሜሪካን መሆኑን ካወቅኩት ሰው ጋር አቧሬ ኢንተርኔት ቤት ወስዳ በስልክ አገናኘችኝ፡፡ በአንድ ጊዜ ቀረቤታ እንዲህ ያለ ነገር ውስጥ ስትከተኝ ደንግጬ ለፖሊስ አመለከትኩ ብሏል፡፡

የተከላካይ ጠበቃ ደርበው በመስቀለኛ ጥያቄ ካሌብ ኤሊያስ ክፍሌ ስለመሆኑ እንዴት አወቅክ፣ እርሷስ ከኤሊያስ ክፍሌ ጋር ስታገናኝህ ምን አለችህ እና ቀደም ሲል እስር ቤት ነው የማውቃት ብለሃል አሁንስ አንድ ላይ ታስራችኋል ሲሉት ” የካሌብ ሥም ኤሊያስ መሆኑን ፖሊስ ነው የነገረኝ፤ ከኤሊያስ ጋር በስልክ ስታገናኘኝም ይህ ሰው ከውጭ የሚረዳን ነው ነው ያለችኝ፡፡ ለፖሊስ አመልክቼ ስላሳሰርኳት
እኔ አልታሰርኩም፣ የወንዶችና የሴቶች እሥር ቤት የተለያየ ስለሆነ ቀደም ሲል በታሰርኩበት ጊዜ አንድ ላይ አልነበርንም ነገር ግን ከእርሷ ጋር በግንቦት 7 ጉዳይ የታሰሩ ወንዶች  ከኔ ጋር ስለነበሩ ስለእርሷ ጉዳይ አውቅ ነበር” ሲል ለዳኞች መልስ ሰጥቷል፡፡

የዐቃቤ- ሕግ 5ተኛ ምስክር ጸጋዬ አዱኛ የወረዳ 5 ጸጥታ አስተባባሪ መሆኑን ገልጾ ለግል ጉዳዬ ወደ ፖሊስ ጣቢያ አምርቼ በነበረበት ጊዜ ውብሸት ታዬ በፍላጎቱ ያለምንም ተጽዕኖ ከኢሜሉ ላይ በእንግሊዝኛ 50፣ በአማርኛ ደግሞ 20 ሠነዶችን ፕሪንት እያደረገ ሲያወጣ በታዛቢነት ተመልክቼ በእያንዳንዱ ገጽ ጀርባ ላይ ስለመታዛቤ ፈርሜያለሁ ያለ ሲሆን ፣ 6ተኛው የዐቃቤ ሕግ ምስክር አቶ ገብረመስቀል በድንጋጤ ድምፃቸው እየተርገበገበ እና የሽምደዳ ንግግር በማድረግ ፣ በ5ተኛ ተከሳሽ ርእዮት ዓለሙ ሰኔ 2003 ዓ.ም  ከቀኑ 8፡00 ሰዓት በፖሊስ ጣቢያ ቢሮ ቁጥር 26   ዘና ብላ፣ ሳትጨናነቅ፣ ያለምንም ተጽዕኖና አስገዳጅነት ከኢሜሏ ላይ የእንግሊዝኛ እና የአማርኛ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው 149 ሠነዶችን ፕሪንት እያደረገች ስታወጣና ፊርማዋን ስታስቀምጥ ተመልክቻለሁ ብለዋል።

የ5ተኛ ተከሳሽ የእርዮት ጠበቃ ሞላ ዘገየ ለምስክሩ “አለመጨናነቋን ደጋግመው ተናግረዋል ለመሆኑ ሳይኮሎጂስት ነዎት፣ 149 ሠነዶችን ይዘት አይቻለሁ ብለዋል ለመሆኑ አንብበውታል፣ ኢሜሉስ ለምን እንደተላከ ከማን እንደተላከ ተመልክተዋል?” ሲሉ መስቀለኛ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፤ ምስክሩ በሚንቀጠቀጥ ድምጽ አለመጨናነቋን ፊቷን ከፊቷ ነው የተረዳሁት፣ በእርግጥ ሠነዶችን አላነበብኩም ርዕሶችን ብቻ ተመልክቼ ነው ይዘቱን የተረዳሁት፣ኢሜሉ ከማን ለምን እንደተላከ እኔ አላውቅም” ሲሉ ጠበቃው ጥያቄዮን ጨርሻለሁ አሉ፡፡

ዐቃቤ- ሕግ በ9ነኛ የምስክርነት ተራ ቁጥር የተቀመጡትን ወ/ሪት ሣምራዊት ፍሰሃ በማቅረብ ያስመሰከረ ሲሆን ከእርዮት ጋር ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ እንደሚተዋወቁና እንደሚቀራረቡ በመግለጽ ርእዮት ልደት፣ ምርቃት የመሳሰሉ ማህበራዊ ጉዳዮች ሲኖራት እንደጓደኝነታችን ካሜራ  ትዋሰኝ ነበር ብላ መስክራለች፡፡

ዐቃቤ- ሕግም የሰው ምስክር ማስረጃ ማጠናቀቁን ገልፆ ” ፍርድ ቤቱ በሚሰጠኝ ቀጠሮ የድምጽና የተንቀሳቃሽ ምስል ማስረጃዎቼን አቀርባለሁ ያለ” ሲሆን ፤ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው “ለፍርድ ቤቱ የድምጽና የምስል ማስረጃ የተባሉትን ቀደም ብሎ እንዲደርሳቸው፣ ኪኢንተርኔት ነው የወጡት የተባሉት ሠነዶች የትኛው ሠነድ ለየትኛው ተከሳሽ እንደሆነ ዐቃቤ- ሕግ በግልጽ አላስቀመጠም፣ ተከሳሾች በፖሊስ ጣቢያ ከ3 ወር በላይ ታስረው በተጽዕኖ፣ በማስፈራራት እና በግርፋት የሰጡት ቃል ለፍርድ ቤቱ እንደማስረጃ መቅረቡ አግባብነት ስለሌለው ውድቅ ይደረግልን” በማለት ያቀረቡትን ጥያቄዎች ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

የ5ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሽ የርእዮት ጠበቃ ሞላ ዘገየ ከደንበኛዬ ኢሜል ወጣ የተባለው የእንግሊዝኛ ሠነድ የአማርኛ ትርጉም መፋለስ ስላለውና እኛ ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል ፍርድ ቤቱ በሚያስተረጉምበት የትርጉም ቤቶች በኩል ይተርጎምልን ብለው ያቀረቡት ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ- ሕግ ያስተረጎመው የሕግ ፈቃድ ባለው ትርጉም ቤት ስለሆነ ችግር የለውም ነገር ግን ተፋለሰ የምትሉትን ለይታችሁ አቅርቡና ወደፊት የሚታይ ይሆናል በማለት የድምጽና የምስል ማስረጃዎችን ለመመልከት ለህዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም  ቀጠሮ ሰጥቷል፡