ኢሳት ዜና:-በብዙ ሚሊዮኖች ዶላር ወጥቶበት እንዲታተም በተደረገው የስምንተኛ ክፍል የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት መጽሀፍ ውስጥ “ተማሪዎችን ሰላማዊ ሰልፍ እንዲያደርጉ የሚያበረታቱ ጽሁፎች ተካትተዋል” በሚል ምክንያት፣ ተማሪዎችና መምህራን የመጽሀፉን አንዳንድ ገጾችን ቀደው እንዲያቃጥሉ ታዘዙ ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው መጽሀፉ እጅግ ውድ በሆነ ዋጋ ታትሞ ወደ አገር ውስጥ የገባ ነው።
መጽሀፉ ባለፈው መስከረም ወር በሚታደልበት ጊዜ ተማሪዎች መጽሀፉን ቀድደው ቢገኙ 100 ብር እንደሚቀጡ በመምህራን በኩል ተነግሮአቸው ነበር። የአማራ ክልል ባለስልጣናት ተማሪዎችና መምህራን መጽሀፉን ገጽ 103 እና 104 እንዲቀዱ ሲያዝዙ፣ ተማሪዎችና መምህራን “ይህን መጽሀፍ ብትቀዱ 100 ብር ትከፍላላችሁ ብላችሁናልና በአዋጅ መጽሀፉን ቅደዱ ተብሎ እስካልተነገረን ድረስ፣ ነገ ደግሞ መጽሀፉን ቀዳችሁዋል በሚል ልንከሰስ ስለምንችል አንከፍልም “የሚል መልስ በትምህርት ቤት ርእሳነ መምህራን አማካኝነት ልከዋል።
በሁኔታው ግራ የተጋቡት ባለስልጣናት መጽሀፉ በጅምላ እንዲሰበሰብ እንዲደረግ መመሪያ ካወረዱ በሁዋላ፣ በምእራፍ 10፣ ገጽ 103 እና 104 የሰፈሩት ጽሁፎች ተቀደው እንዲቃጠሉ ተደርጓል።
“ተውለደሬ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ሰፈር” በሚለው ምእራፍ ስር ተውለደሬ እና ኩሸሽሌ የተባሉ ሁለት ወረዳዎችን በመልካም አስተዳዳር እና በዲሞክራሲያዊ ስርአት ያላቸውን ልዩነት ያብራራል።
የሁለቱን ወረዳዎች ልዩነት ለማነጻጸርም አቶ አልቃድር አማን የተባሉ የመቂት ወረዳ ተወላጅ በእማኝነት ቀርበዋል። አቶ አልቃድር ለ26 አመታት በውጭ አገር ከኖሩ በሁዋላ ወደ አገራቸው ተመልሰው በኩሸሺሌ ወረዳ ውስጥ ስራ ለመስራት ፈልገው ሙስናውና ቢሮክራሲው አላሰራ ስላላቸው ስራቸውን ወደ ተውለደሬ በማዞር ለመስራት መገደዳቸውን ጽሁፉ ይገልጣል ።
በገጽ 104 ላይ ደግሞ “ዲሞክራሲ ባልሰፈነበት አገር መከባበር መተማመን መደማመጥ አይኖርም፣ ይልቁንም የጥቂቶች አምባገነንነት ስለሚደነድን የብዙሀን መጎዳት የማይቀር ነው። ብዙሀኑ ለጋር እድገት ሚያደርጉት መነሳሳት ይቀጭጫል። ማህበራዊ ልማትም ይጠፋል። በተቃራኒው ግን የዲሞክራሲ ስርአት መገንባት ተከታትሎም የጋራ መግባባት መፈጠርና የመልካም አስተዳደር መስፈን ማህበራዊ ፍትህ እንዲመጣና ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲከተል ስለሚያደርግ አገር ይበለጽጋል። የጋራ መግባባትና የመልካም አስተዳደር መስፈን መልሶ ዲሞክራሲውን ስለሚያጠናክር እድገቱ ቀጣይነት ይኖረዋል። እኒህ ውጤቶች ግን በራሳቸው የሚመጡ አይደሉም። በህብረተሰቡ ውስጥ እኒህ ውጤቶች እውን እንዲሆኑ የሚያደርግ ጠንካራ ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል። ያለንቁ ህዝባዊ ተሳትፎ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ተጠናክሮ አይገነባም፣ መልካም
አስተዳዳርም በዘላቂነት ሊሰፍን አይችለም። እነዚህ ባልተሟሉበትም ልማትና መልካም አስተዳደር ሊሰፍን አይችልም ” የሚል ሰፍሯል።
ለገጾች መቀደድ ዋና መክንያት የሆነው “ዲሞክራሲና መልካም አስተዳዳር ባልሰፈነበት የኩሸሺሌ ወረዳ ነዋሪ ብትሆን ምን እርምጃ ትወስዳለህ?” የሚለው ጥያቄ በርካታ ችግሮችን ይዞ የሚመጣ በመሆኑ ነው በማለት በደቡብ ጎንደር መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር የሆኑት አቶ አበባው አለፈ ይናገራሉ።
መንግስት በአገኘው አጋጣሚ ሀሉ ስለመልካም አስተዳዳርና ዲሞክራሲ እንዳይነሳበት ጥረት እንደሚያደርግ የገለጡት አቶ አበባው፣ ብዙ ሚሊዮኖች ፈሶበት እንዲሰራጭ የተደረገው መጽሀፍ እንደገና እንዲታተም ሊደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የመጽሀፉን የመጀመሪያ ቅጅ ያዘጋጁት አቶ ሸዋ ቀና ቸርነት፣ አቶ ቦጋለ ስብሐቱ፣ አቶ አሰግደው ተስፋዬ፣ አቶ ተስፋዬ ክፍሉ፣ አቶ ጌታቸው በለጠ፣ ወ/ሮ ጸሀይ መላኩ፣ ወ/ሮ ውዳላት ገዳሙ፣ ወ/ሮ ዬዝና ወርቁ፣ ወ/ሮ አገረደች ጀማነህ፣ አቶ ብቃለ ስዩም እና አቶ የሻው ተሰማ ናቸው።
ኢሳት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች በሲቪክ ትምህርት ክፍለ ጊዜ የኢህአዴግን ፖሊሲ የሚተች አስተያየት ሲያቀርቡ በካድሬ መምህራን ተጠርተው እንደሚጠዬቁ መዘገባችን ይታወሳል።