ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)
ዛሬ በጎንደር ከተማ 1ሺህ በላይ ነዋሪ በታደመበት ስብሰባ፣ የወልቃይት የአማራ ማንነት አስተባባሪ አባላት እንቅስቃሴያቸውን ለህዝብ ማሳወቃቸው ተገለጸ።
በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መንግስት እየተዋከቡ የሚገኙትና በብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ድጋፍ ያጡት የወልቃይት የአማራ ማንነት አስተባባሪ ኮሚቴ አባለት በብአዴን የተከለከለ ስብሰባ ዛሬ በጎንደር ከተማ ከህዝቡ ጋር ማካሄዳቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አለምነት መኮንን በጎንደር ከተማ ከንቲባ አማካኝነት ስብሰባው እንዳይካሄድ ጥረት ቢይደርጉም በጎንደር ሽማግሌዎች ቆራጥነትና በጎንደር ወጣቶች የተቀናጀ ቅስቀሳ አዳራሽ ሞልቶ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲመለሱ የተገደዱበት ስብሰባ ሊካሄድ ችሏል።
በህወሃት መገናኛ ብዙሃን የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲካሄድባቸው የነበረው የኮሚቴው አባላት ለጎንደር ህዝብ ብሶትና ስቃያቸውን በሰፊው አስረድተዋል።
የወልይቃይት ህዝብ ላለፉት 25 አመታት ያለውዴታና ያለፍቃዱ ማንነቱን ተነጥቆ በስቃይ እየኖረ መሆኑን የገለጹት የኮሚቴው አባላት፣ ወደትግራይ ክልል መጠቃለላቸውን ሲቃወሞ የነበሩ ሰዎች በሌሊት እየተወሰዱ መገደላቸውን፣ የወልቃይት ሴቶች ባል አልባ ሆነ መቅረታቸውን በመዘርዘር የተፈጸመባቸውን የዘር ማጽዳት ወንጀል በሰፊው አብራርተዋል።
የጎንደር የሃገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች በሰሙት ዜና ልባቸው መሰበሩን በመግለጽ በየትኛውም የትግል እንቅስቃሴ ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል።
የትግራይ የቀድሞ ሃገረ ገዥ ልዑል ራስ መንገሻ ስዩምን ጨምሮ የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መስራችና አመራር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ አቶ ግደይ ዘራጽዮን፣ አቶ አሰግደ ገብረስላሴና አቶ ገብረመድህን አረአያ፣ የወልቃይት ጠገዴና ጸለምት ድንበርና ማንነት የአማራ መሆኑን በአደባባይ እየገለጹ ባሉበት በዚህ ወቅት የትግራይ ክልል ባለስልጣናት መጠነ ሰፊ አፈና በማከናወን ላይ መሆናቸው ታዉቋኣል።
በቅርቡ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አባይ ወልዱ የወልቃይት የአማራ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት ላይና እንቅስቃሴን በሚሳተፉ ወገኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስዱ ማስጠንቀቃቸውን ይታወሳል።