በኢትዮጵያ የሚገኘው የኑዌር ወጣቶች ህብረት የደቡብ ሱዳን መልዕክተኛን ሹመት ተቃወመ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የሚገኘው የኑዌር ወጣቶች ህብረት የደቡብ ሱዳን መልዕክተኛ አድርጎ የሾማቸውን አምባሳደር ተቃወመ።

የሃገሪቱ መንግስትም የመልዕከተኛው ጀምስ ሞርጋንን ሹመት በአስቸኳይ እንዲሰርዝ ህብረቱ መጠየቁን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ ሃሙስ ከአዲስ አበባ ዘግቧል።

በልዩ መልዕክተኛው ላይ ተቃውሞ ያቀረበው የኑዌር ወጣቶች ህብረት አምባሳደር ጀምስ ሞርጋን የተባበሩት ኢትዮጵያ አርበኞች ግንባር ከተባለ አማጺ ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ምክንያት ማቅረቡንም ጋዜጣው አስነብቧል።

በኬንያ ለሶስት አመት ያህል የደቡብ ሱዳን ምክትል አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ጀምስ ሞርጋን በሃገሪቱ ቆይታቸው ቶዎዝ ፓልቻይ በተባለ የአማጺ ቡድን አመራር ተመልክምለው ለግንባሩ ኢትዮጵያን ሲሰልሉ መቆየታቸውን ህብረቱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የትጥቅ ትግልን ያካሄዳሉ የሚባሉ የጋምቤላ አማጺ ቡድኖች በጁባ መንግስት ድጋይ ይደረግላቸዋል የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁንና፣ የተባበሩት ኢትዮጵያ አርበኞች ግንባት አመራር የሆኑን ፓል-ቻይ የቀረበባቸው መረጃ መረሰረ ቢስ እንደሆነ ያስተበበሉ ሲሆን በጋምቤላ ክልል የሚገኙ አማጺ ቡድኖች ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በድብቅ አማጺያንን ይረዳሉ የሚል ቅሬታን ያቀርባሉ።

የልዩ መልዕክተኛው ሹመት የተቃወመው የኑዌር ወጣቶች ህብረት የምባሳደር ጀምስ ሞርጋን ሹመት የኢትዮጵያንና የደቡብ ሱዳንን ግንኙነት ሊያሻክር እንደሚችል አክሎ አሳስቧል።

ተቃውሞውም ለደቡብ ሱዳን መንግስት ያቀረበው ህብረቱ የኢትዮጵያ መንግስትም የልዑኩን ሹመት ከመቀበል እንዲቆጠብ መጠየቁን ሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ በዘገባት አስነብቧል።

ልዩ መልዕክተኛ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታም የዲፕሎማቲክ መብታቸውን ተጠቅመው ለአማጺ ቡድኑ እንደሚሰልሉ ህብረቱ ያለውን ስጋት አክሎ ገልጿል።

የግንባሩ መሪ ፓል-ቻይ በቀድሞ መንግስት ጊዜ የጋምቤላ ክልል አስተዳዳሪና የክልሉ የጸጥታ ሃላፊ እንደነበሩ ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያም ሆነ የደቡብ ሱዳን መንግስት የሰጡት ምላሽ የለም።