አቶ ሌንጮ ለታ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ አንድነት መንገድ የጠረገ መሆኑን ገለጹ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የኦሮሚያ ክልል የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የኦሮሞ አንድነት ያረጋገጠና ለእውነተኛ ኢትዮጵያ አንድነት መንገድ የጠረገ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ አቶ ሌንጮ ለታ ገለጹ።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባት መስራችና ምክትል ዋና ጸሃፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ፕሬዚደንት የሆኑት አቶ ሌንጮ ለታ፣ ይህንን የተናገሩን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።

ለስራ ጉዳይ ከአውሮፓ ወደ ዋሽንግተን ብቅ ያሉትና በኢሳት ስቱዲዮ ተገኝተው ቃለ-ምልልስ የሰጡት አቶ ሌንጮ ለታ፣ በሃገር ቤት በትግል ለሚገኙ የኦሮሞ ወጣቶች የማህበረሰብ አባላት በኦሮምኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት ትግላቸው ፍሬ እያፈራ መሆኑን ገልጸዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም አብረዋቸው ሊቆሙ ተዘጋጅተዋል ብለዋል።

በቅርቡ ለጠ/ሚኒስትር ሃይለማሪያም በጻፉት ደብዳቤ፣ የሃገሪቱ ጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ፣ እንዲሁም የሃገሪቱ የደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ከስልጣን እንዲነሱና በኦሮሞ ህዝብ ላይ ባደረሱት ግድያ እንዲጠየቁ ያሳሰቡት አቶ ሌንቾ ለታ በዚህ ዙሪያ ለተነሳባቸው ጥያቄ በቂ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኦሮሞ ህዝብ ገንጥሎ አዲስ ሃገር መፍጠር ዛሬ ከጊዜው ጋር የማይሄድ አስተሳሰብ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ጥላ ስር ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን መብት በመታገል ዲሞክራሲያዊት ሃገር ለመፍጠር እንደሚቻል የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታ፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ) በዚህ መንፈስ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ለመስራት መንቀሳቀሱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ችግር ሰፊና ውስብስብ በመሆኑ፣ አንድ ፓርቲ ብቻ ስለማይፈታው በጋራ መምከርና ለዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በጋራ መታገል እንደሚገባም አሳስበዋል።

አሁን በኦሮሚያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ የኦሮሞ ህዝብ መብቱ እንዲከበር ያቀረበው ህጋዊ ጥያቄ በመሆኑ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ስጋት ሊሆን እንደማይገባ የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታ፣ የኦሮሞ አንድነትን ያመጣው ይህ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ አንድነትም እንደሚበጅ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል። ምላሽ በተነፈገና ጥቃቱ በበረታ ቁጥር የማይፈለግ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዋሽንግተን ዲሲ ኢሳት ስቱዲዮ ተገኝተው ቃለ-ምልልስ ያደረጉት አቶ ሌንጮ ለታ በትግልና በመስዋዕት ውስጥ ለሚገኙ የኦሮሞ ወጣቶችና በጥቅል በማህበረሰቡ በኦሮምኛ ቋንቋ ባስተላለፉት መልዕክት “የተከፈለው መስዋዕትነት ብዙ ቢሆንም፣ ብዙ ውጤቶች አስመዝግባችኋል፥ ወደ ድልም እየወሰደን ነው። ድምጻችሁ በጋራ ተሰምቷል። ኢትዮጵያውያንም ከጎናችሁ ሆነው በህብረት ለመታገል ተዘጋጅተዋል። በርቱ ድል ከእናንተ ጋር ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዛሬ 46 አመት ኒውዮርክ ከሚገኘው ራቸስተር ዩኒቨርስቲ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ዲግሪያቸውን በመውሰድ ወደኢትዮጵያ የተመለሱትና ጥቂት ጊዜያት በመንግስት ስራ ላይ ቆይተው ቀሪ ህይወታቸውን በፖለቲካ አለም ያሳለፉት አቶ ሌንጮ ለታ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በትግልና በሽግግር ሂደት ውስጥ ያለፉበትን ጎዳና እንዲሁም ከህወሃትና ከሻዕቢያ ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ሂደቱን ተከትሎ ስለመጣው ሁኔታ ዘርዝረዋል።

ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ቀድሞ አዲስ አበባ ይደረሰው የሻዕቢያ ሰራዊት ለ 5 አመታት ያህል በኢትዮጵያ ለህወሃት ድጋፍ ሲያደግ መቆየቱን የገለጹት አቶ ሌንጮ ለታ፣ ህወሃት የመገንጠል አጀንዳ እንዲተው ግፊት የተደረገበት በሻዕቢያ እንደነበረም  አመልክተዋል። ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ህልውና ተከብሮ እንዲቀጥል ግፊት ያደርግ እንደነበርም አስታውሰዋል።

ህወሃትና ሻዕቢያ ድል ሲቀናቸው ኦነግ ለውጤት ያልበቃበትን ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች የዘረዘሩት አቶ ሌንጮ ለታ የኦነግ ትግል ከደርግ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሶማሊያና ከሱዳን አማጺያን ተፅዕኖ ጋር ጭምር እንደነበር አመልክተዋል።

በዘግናኝነቱ የሚጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ የተወነጀለበት የበደኖ ጭፍጨፋ በተመለከተ አቶ ሌንጮ ለታ በሰጡት ምላሽ፣ ኦነግ እጁ ከደሙ ንጹህ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በሃሰት የተቀነባበረ ግድያ ነው ሲሉ ተናግረዋል።