ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ጉዳትን እያደረሰ ያለው የድርቅ አደጋን ተከትሎ ሃገሪቱ ለወጪ ንግድ የሚሆን የጥርጣሬ ምርት ማቅረብ አለመቻሏን የንግድ ሚኒስቴር ሃሙስ አስታወቀ።
ድርቁ ባስከተለው ጉዳትም ባለፉት ሰባት ወራት የወጪ ንግዱ የ126 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን የሚንስቴሩ ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።
ይኸው በስድስት ክልሎች ጉዳትን እያደረሰ ያለው አደጋ ሃገሪቱ ከግብርና ምርቶች በምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን ያሳደረ ሲሆን የተጠበቀውን ያህል ምርት አለመገኘቱንም የንግድ ሚኒስቴር መግለጹን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ሀገሪቱ ባለፉት ሰባት ወራቶች ለውጭ ሃገር ገበያ ያቀረበችው የጥራጥሬ ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በመጠን በግማሽ መቀነሱንም የንግድ ሚኒስቴር አክሎ ገልጿል።
ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ አጋልጦ የሚገኘው የድርቅ አደጋ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይም አሉታዊ ተጽዕኖን ሊያሳድር ይችላል በማለት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ማሳሰባቸው ይታወሳል።
በጥራጥሬ ወጪ ንግድ ላይ የታየው የውጭ ምንዛሪ ማሽቆልቆል በቡናና በሌሎች የግብርና ምርቶች ላይም ተመሳሳይ ኪሳራን ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል።
የሀገሪቱ የግብርና ንግድ ገቢ እያሽቆለቆለ መምጣትም እየተባባሰ ባለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ላይ ተጨማሪ ጫናን እንደሚያሳድር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች የእርዳታ ተቋማት ድርቁ በሰዎች ላይ እያደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ በሃገሪቱ የጤና መሰረተ-ልማት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እያደረሰ እንደሚገኝም ይገልጻሉ።
ለተረጂዎች የሚሆን በቂ የእርዳታ እህል በወቅቱ ወደሃገሪቱ ባለመግባቱም ከቀጣዩ ወር ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊዎች ያለምንም ድጋፍ ይቀራሉ ተብሎ ስጋት መኖሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዳግም አሳስቧል።
የመንግስት ባለስልታናት በበኩላቸው ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ አይሆንም ሲሉ ስጋቱን አስተባብለዋል።