ኢሳት (ጥር 12 ፥ 2008)
የአውሮፓ ፓርላማ በወቅታዊ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ለሰዓታት የፈጀ ክርክርን በማካሄድ ለውይይት የቀረቡ በርካታ የእርምጃ ሃሳቦችን ሃሙስ አጸደቀ።
ይኸው የፓርላማ አባላቱ ያጸደቁት ሃሳብ የተለያዩ አንቀጾች ሲኖሩት የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአውሮፓ ህብረት በሃገሪቱ መወሰድ ስለሚገባው እርምጃዎችና ፖሊሲዎች ግብዓት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ተከትሎ የተካሄደው ይኸው ልዩ የመወያያ መድረክ በሃገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰዎችንና ግድያዎችን በዋነኝነት ትኩረት ሰጥቶ መወያየቱን ለመረዳት ተችሏል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶችና አመራሮች እንዲሁም ጋዜጠኞች ለእስርና እንግልት እየተጋለጡ መምጣታቸው አሳሳቢ መሆኑም በፓርላማ አባላቱ የጸደቀው ሰነድ አመልክቷል።
በፓርላማ አባላቱ የተሰጡ ማሳሰቢያዎችንና ማስተካከያዎችን መሰረት በማድረግም የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ሊወስደው ሰለሚገባ እርምጃ በቅርብ መረጃዎች ይፋ ያደአርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በርካታ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ህብረቱ ዝምታውን በመስበር በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድና አቋሙን እንዲገልጽ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወቃል።
ይህንኑ አለም አቀፍ ዘመቻና በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ያለውን ግድያና እስራት ተከትሎ ሃሙስ የተካሄደው ልዩ የፓርላማ አባላት መድረክ በሃገሪቱ ያለው ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ መብት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አመልክቷል።
በዋቢነት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና እስራቶች ያቀረበው የአውሮፓይ ፓርላማ ቡድን መንግስት እየወሰደ ያለው የሃይል እርምጃ ከበርካታ አለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ተቃውሞ ማስከተሉንም ዘርዝሯል።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራትም በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሰፊ ማብራሪያን ማቅረባቸውም ተገልጿል።