ታኀሳስ ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአዲስ አበባ 26 ኪሜ ርቅት ላይ በምትገኘዋ ሱሉልታ ሁሉም የህብረተሰብ ከፍል የተሳተፈበት ከባድ ህዝባዊ ተቃውሞ ተካሄዷል። የጸጥታ ሃይሎች በወታደራዊ ሄሊኮፕተሮች ታጅበው ቅኝት ሲያደርጉ ውለዋል። በህዝቡ ላይ ፍርሃት ለመልቀቅ የተደረገው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።
ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም እና ጎንደር የሚወስደው መንገድ ለተሽከርካሪ ዝግ ሆሮ አርፍዷል። የጸጥታ ሃይሎች በርካታ ወጣቶችን ይዘው አስረዋል። ተመሳሳይ ተቃውሞዎች በአሌሊቱ፣ አምቦ፣ ወለጋ እንዲሁም በምእራብ ሸዋ ሜታ ሮቢ ከተሞች ተካሂደዋል።
በአዲስ አበባ በማንኛውም ጊዜ ህዝባዊ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል በሚል መንግስት ተጨማሪ ሰራዊት ከተለያዩ የጦር ካምፖች ወደ አዲስ አበባ እያስገባ ነው። ህዝባዊ አመጹን በመቆጣጠር በኩል በመንግስት የደህንነት ሃላፊዎች መካከል የሃሳብ ልዩነት መፈጠሩም ታውቋል። ችግሩን አሳንሶ ማዬቱ በሁዋላ ላይ ልንቆጣጠረው ከማንችለው ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚሉና ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት የሚያደርጉ ሃይሎች በአንድ በኩል፣ የምንወስደው እርምጃ አመጹን ይበልጥ አቀጣጥሎ የመንግስትን ህልውና አደጋ ላይ ይበልጥ ይጥለዋል የሚሉ የደህንነት ሹሞች በሌላ በኩል ሆነው መወሰን ተስኗቸው እየተሟገቱ ነው።
በሌላ በኩል በህወሃቱ ከፍተኛ አመራር አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን፣ ለኢህአዴግ ደጋፊ ሚዲያዎች እና ለመንግስት የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በኦሮሚያ የተከሰተውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በተመለከተ መስጠት ስለሚገባቸው መረጃ አቅጣጫ ያስቀመጠበት ሰነድ ኢሳት እጅ ገብቷል። ጽ/ቤቱ በዛሬው እለት ባሰራጨው ጹሑፍ መሰረት የማስተር ፕላን ጥያቄው ተገቢና የህዝብ ጥያቄ መሆኑን
እንዲያንጸባርቁ ነገርግን እሱን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በተደራጁ ኃይሎች ሕገመንግስቱን ለመናድ ያለመ መሆኑን እንዲያሳዩ ያዛል፡፡ የጉዳት መጠንን በቁጥር መግለጽን በተመለከተ ቁጥርን ማስተባበል እንደማይገባ እንዲሁም ረብሻው እየሰፋ እንደሄደ የማሳየት ፍላጎት ያላቸው ወገኖች መኖራቸውን በመገንዘብ ረብሻው እየቀነሰና ሕዝቡ ወደቤቱ በመግባቱ ላይ መሆኑን መግለጽ እንደሚገባ አሳስቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግስት ታጣቂዎች በሰንዳፋ እና አካባቢዋ የሚኖሩ የሌሎች ብሄር ተወላጆች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ማታ ማታ እያስፈራሩ ነው ። ነዋሪዎች እንደተናገሩት የመንግስት ታጣቂዎች ክልሉን ለቃችሁ ካልወጣችሁ እርምጃ እንወስዳለን በማለት እያስፈራሩና ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ሊያጋጩን እየሞከሩ ነው ብለዋል
በተመሳሳይ ዜናም በቡራዩ፣ በአስኮና ሌሎችም ትምህርት ቤቶችና የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታዎች መንግስት ያሰማራቸው ካድሬዎች የኦሮሞን ህዝብ የሚሰድቡ ጽሁፎችን እየበተኑና ግድግዳዎች ላይ እየለጠፉ ነው። ድርጊቱ ሆን ተብሎ ግጭት ለመፍጠር መሆኑን ተማሪዎች ይናገራሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሚኒስትሮች በት/ሚኒስቴር አዳራሽ ተሰብስበው የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል። ሚኒስትሮቹ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች እንዲቀጥሉ እንዲነግሩ፣ ሰራተኞቻቸውን ታህሳስ 7 ቀን 2008ዓ ም በ10 ሰዓት ሰብስበው እንዲያወያዩ፣በኦሮሚያና አማራ የተፈጠረውን ተቃውሞ መንግስት እንደተቆጣጣጠረው ለህ/ሰቡ እንዲነግሩ እንዲሁም ችግር የተፈጠረው በግንቦት 7 ፣ ኦነግና አርበኞች ግንባር እንደሆነና የህዝብ ጥያቄ እንዳልሆነ እንዲናገሩ ታዘዋል።