ኀዳር ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ለብዙ ዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተነጥለው ሲጉላሉ የነበሩት 9 ሽህ ቤተ-እስራኤላዊያን ወደ እስራኤል እንዲገቡ በእስራኤል መንግስት ፍቃድ ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው በተስራኤላዊያኑ ተናግረዋል።እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ1970 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ እስራኤል እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ቤተ እስራኤላዊያን ከሰላሳ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሁኔታዎች ጉዟቸው መደናቀፉ ያሳዘናቸው ሲሆን ዘግይቶም ቢሆን ውሳኔ መሰጠቱን በጸጋ ተቀብለውታል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ኢትዮ-እስራኤላዊያን በእስራኤል ማኅበረሰብ መድሎና መገለል እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ወጣቱ ቤተ- እስራኤላዊ አቭራል እስካሁን ድረስ በጋዛ በሃማስ ታግቶ የሚገኝ ሲሆን የእስራኤል መንግስት እሱን ለማስለቀቅ ጥረት ያለማድረጉ የቀለም መድሎ ዘረኝነት አሰራር ነው ሲሉ ቤተእስራኤላዊያን ሁኔታውን በመቃወም መተላለፊያ ኬላዎችን በተቃውሞ ሰልፍ መዝጋታቸውና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸው አይዘነጋም።
በቅርቡ የእስራኤል የስታስቲክስ መረጃ ቢሮ ቤተ እስራኤላዊያን የሚያገኙት ክፍያ ከሌላው እስራኤላዊ እንደሚያንስና በዚህ ምጣኔ ሃብታዊ ችግር ምክንያት የፍቺ ቁጥር መጨመሩን ዘታይም ኦፍ እስራኤል አክሎ ዘግቧ።