ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚወስዱ መንገዶችን ዘጋች

ኀዳር ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ባለፈው አርብ በኬንያ ፖሊስና እና በኢትዮጵያ ወታደሮች መካካል በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 3 የኬንያ ፖሊሶች እና 4 የኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የሚወስዱ መተላለፊያ መንገዶችን ዘግታለች። ሞያሌ፣ ሶሎሎ፣ ፎሮሌ፣ ዱካና እና ኢሌሪቲ የተባሉት የድንበር መተላለፊያዎች ተዘግተዋል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች የኦነግ ታጣቂዎችን ለመዋጋት በሚል ወደ ኬንያ በመግባታቸው የተኩስ ልውውጡ ተደርጓል። በድንበር አካባቢ አሁንም ውጥረት መኖሩ ተዘግቧል። ግጭቱን ተከትሎ ኬንያ ወታደሮቿን ሶሎሎ ወደ ሚባለው የድንበር ከተማ ልካለች። ኢትዮጵያም እንዲሁ ጦሯን ወደ ድንበር በማስጠጋት ቅኝት እያካሄደች ነው። ካለፈው አርብ ወዲህ የተካሄደ ግጭት ባይኖርም ውጥረቱ ግን እንዳለ ነው ሲሉ የኬንያ ጋዜጦች የአካባቢ ባለስልጣናትን እየጠቀሱ በመዘገብ ላይ ናቸው።
ግጭቱን በተመለከተ በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን የተባለ ነገር የለም።