ድርቁ ከ1977ቱ ያልተናነሰ ነው ሲሉ አርሶአደሮች ተናገሩ

ኀዳር ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በወሎ፣ቆቦና ዋግ ህምራ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች የዘንድሮው ድርቅ ከ1977ቱ ያልተለየ ነው በማለት ለኢሳት ተናገሩ፡፡
ተጎጂዎች በድርቁ በርካታ ሃብት ንብረታቸውን በመጨረሳቸው ባዶ እጃቸውን እንደቀሩ ይናገራሉ፡፡የገዢው መንግስት ሚዲያዎች በድርቁ የሞተ ሰው የለም በማለት ለማስተባበል ቢሞክሩም ተጎጅዎቹ ‹‹ ከሃብታችን ባሻገር ልጆቻችን እየተነጠቅን ነው፡፡ ›› በማለት በተጨባጭ ያለውን የወቅቱን ችግር ይገልጻሉ፡፡
ድርቁ ዘንድሮ በይፋ በሁሉም አካባቢ ይከሰት እንጅ ባለፉት ሶስት አመታትም በተከሰተው የዝናብ እጥረት ከብቶቻቸውን ለመቀለብ የቤታቸውን ጣሪያ ሳር በመግፈፍ ለመቀለብ እንደተጠቀሙበት ያስታውሳሉ፡፡ የሳር ሃገር የነበረው፣ ሳሩ በማረሩ መሬቱ ባዶ በመሆኑ ለጥጆች እንኳን የሚበቃ ምግብ አለመኖሩን ተጎጅዎች ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ ወራቶች ዝናብ ካልጣለ ከብቶቻቸው እንደሚያልቁና እነርሱም ችግር ላይ እንደሚወድቁ ፍራቻቸውን ይገልጻሉ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብር ወጪ ተደርጎ በየከተማውና በየሴክተር መስሪያ ቤቱ በግዳጅ ለአንድ ወር ሲከናወን የቆየው የብአዴን በዓል በታሰበው መልኩ ውጤት ሳያመጣ ተጠናቋል፡፡ ብአዴን ከባህርዳር ውጭ ያሉ የገጠር ነዋሪዎች መኪና አቅርቦ በአሉን ለማድመቅ ቢሞክርም፣ አብዛናው የባህርዳር ነዋሪዎች እንደሁም የዩኒቨርስቲ መምህራን በበአሉ ላይ አልተገኙም።
በተለይ ለአማራው ህዝብ ቆሚያለሁ የሚለው ብአዴን-ህውሃት ህዳር 3/2008 ዓ.ም በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በተደረገው የቼክ ርክክብ ስነ ስርዓት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዕርዳታ ማድረጉን በክልሉ ሚዲያዎች የተዘገበውን የተመለከቱ የባህርዳር ነዋሪዎች ‹‹ለበዓሉ ሽርጉድ ከመደበው በ10 እጥፍ የሚያንስ ገንዘብ ለሚዲያ ፍጆታ ለማዋል ዕርዳታ ብሎ መስጠቱ አስቂኝ ነው፡፡ ›› በማለት አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡
ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር አላስፈላጊ የካኪ ልብስና ሽርጥ ለበአሉ ታዳሚዎች ለአንድ ቀን ከማልበስ ይልቅ በረሃቡ ለተጎዱ ወገኞች ዕርዳታ ሊውል ይገባ ነበር በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከረሃቡ ዜና ሳንወጣ የሴቭ ዘ ችልድረን የኢትዮጵያ ተወካይ ጆን ግርሃም “ኢትዮጵያ እርዳታ ትፈልጋለች፣ ፊታችንን ልናዞርባት አይገባም” በሚል ርዕስ በአውስትራሊያ ታዋቂ ለሆነው ሄራልድ ሰን ላይ ጽሁፍ አቅርበዋል። ተወካዩ ኢትዮጵያ በ30 አመታት ውስጥ ያልታዬ ድርቅ አጋጥሟታል ብለዋል። አለማፍ እርዳታ ለሶሪያ፣ ኢራቅ፣ የመን፣ ኔፓልና ደቡብ ሱዳን እየተሰጠ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ድርቅ መከሰቱ አሳዛኝ ቢሆንም፣ አለም ፊቱን ሊያዞር እንደማይገባ፣ አውስትራሊያ ከ4 አመታት በፊት እንደሰጠቸው ድጋፍ አሁንም ተመሳሳይ ድጋፍ እንድትሰጥ ተማጽነዋል።
የኢህአዴግ መንግስት አቋም አንዳንድ ተቋማትና ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸውን እንዳይደግፉ እያደረጋቸው ነው። ኢህአዴግ ተከታታይ እድገት ማስመዝገቡን በተደጋጋሚ መናገሩ አሁን በድፍረት ረሃብ አለ ብሎ ለመናገር አሳፍሮታል። በቅርቡ የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ተጠሪ የሆኑት ጌታቸው ረዳ፣ አለማቀፍ ማህበረሰቡ እርዳታ ለማግኘት ሲባል የተረጅዎችን ቁጥር እያጋነነ ያቀርባል በማለት ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ፣ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው ድጋፍ ለመስጠትና በተለይም አለማቀፉ ማህበረሰብ ፊቱን ወደ ሶሪያና ሌሎች ቦታዎች በማዞሩ ክፍተቱን ለመሙላት በአስቸኳይ እንዳይደራጅ እንዳደረገው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያን አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።