ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሂራን ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በለደወይኒ ፣ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮችን ጭኖ ሲጓዝ በነበረ ወታደራዊ ተሽከርካሪ ላይ አልሽባብ ባደረሰው የደፈጣ ውጊያ ጥቃት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ወታደሮች መገደላቸውን የአካባቢውን የዓይን እማኞችን ጠቅሶ ሸበሌ ሬዲዮ ዘግቧል።
ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እስከ ረቡዕ ጠዋት ድረስ በአካባቢው አዲስ ውጊያ መቀስቀሱንና በሁለቱ አንጃዎችና በሕዝቡም መሃከል ውጊያው መቀጠሉን ገልጸዋል። የሶማሊያ ወታደራዊ ጦር አዛዥ የሆኑት መሃመድ ኦማር አደን ከሬዲዮ ሸበሌ ጋር ባደረጉት ቃለመጠይቅ እንደተናገሩት በአልሸባብና በኢትዮጵያ ሰራዊት መሃከል የተደረገው ውጊያ፣ ማክሰኞ ከሰዓት መቆሙንና አልሸባብ ወደ በለደወይኒ ምዕራባዊ አካባቢ ማፈግፈጉን ገልጸዋል።ከአልሸባብ በኩል የተሰጠ ምንም ዓይነት ምላሽ አለመኖሩንም ኦል አፍሪካ አክሎ ዘግቧል።
ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ሄሊኮፕተሮች ሟቾችንና ቁስለኞችን ሲያመላልሱ መታየታቸውን፣ የደረሰውም ጉዳት ከፍተኛ ሳይሆን እንደማይቀር ዘጋባዎች አመልክተዋል። በቅርቡ ግዳጁን አጠናቆ የተመለሰ አንድ ወታደር ለኢሳት እንደገለጸው፣ በሶማሊያ በኢትዮጵያ ሰራዊት ላይ እየደረሰ ያለው እልቂት ዘግናኝ ነው ብሎአል። የሶማሊያ ባለስልጣኖች ሳይቀሩ የኢትዮጵያ ጦር ለቆ እንዲወጣ ይጠይቃሉ ያለው ወታደሩ፣ ጦሩ ለመውጣትም ለመቆየትም በማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ብሎአል። በሶማሊያ የነበረውን ቆይታም ” ሲኦል” ሲል በአጭር ቋንቋ ገልጾታል።