ነኅሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የመኢአድ ፓርቲ የአመራር አባላት በእስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ወጣት ተስፋየ ታሪኩ፣ ቀድም ብሎ በእስር ቤት ውስጥ እየተደበደቡ መሆኑን ለፍርድ ቤት ማመልከቱን ተከትሎ ፣ ፖሊሶች ዘቅዝቀው በጠመንጃው ሳንጃ በሽፋኑ ጀርባውን ደብድበውታል፣ እጁና እግሮቹም ተጎድተዋል። ተስፋየን ፍርድ ቤት አካባቢ እንዳገኘውና መደብደቡን እንደነገረው የገለጸው የመኢዴፓ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ፣ መላው ሰውነቱ ላይ የሚታየው ነገር ጥሩ አይደለም ብሎአል ። ተስፋየ ተክላይ የሚባል የማረሚያቤቱ ሃላፊ እንዲደበደብ ትእዛዝ መስጠቱንም ተናግሯል።
ሌላው የአመራር አባል አብርሃም ጌጡም እንደሁ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበት፣ ለ4 ቀናት ያክል ራሱን ስቶ ነበር። ግራ ጆሮው በከፍተኛ ሁኔታ መጎዳቱን፣ ለመንቀሰቀስ አለመቻሉንም የቅርብ ዘመዶቹ ገልጸዋል። ቤተሰቦቹ አብርሃምን ለመጎብኘት ላለፉት 2 ወራት ሙከራ ቢያደርጉም ሊሳካላቸው አልቻለም። አብርሃም ፍርድ ቤት ይቅረብ አይቅረብም ለማወቅ አለማቻላቸውን የአለም ህዝብ እንዲያውቅላቸውና ግፊት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።
በእስር ቤት ያሉት አመራሮች ህለውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን በተደጋጋሚ ለፍርድ ቤት ቢያቀርቡም ዳኞች ግን፣ ይህን እኛን አይመለከተንም ከማለት ውጪ ይህ ነው የሚል መፍትሄ ሊሰጡ አልቻሉም።