የኢትዮጵያ ሰራተኞች የውጭ አገር ኩባንያዎች ባሪያዎች ሆነዋል ተባለ

ነኅሴ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቢቢሲ ሬዲዮ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክቶ በሰራው ዘገባ ፣ የአገሪቱ ሰራተኞች በአለም ላይ እጅግ ዝቅተኛ የሆነ ክፍያ ከሚያገኙ አገሮች ቀዳሚ መሆናቸውን ጠቅሶ፣ የውጭ አገር ኩባንያዎች ሰራተኞቹን እንደ ባሪያ እንደያዙዋቸው ገልጿል።
ከ11 ሚሊዮን በላይ ስራ አጥ ባለበት የሰራተኛውን የመጨረሻ የክፍያ ወለል ማስተካከል ፈታኝ መሆኑን የገለጸው ቢቢሲ፣ ወጣቱ በ50 ዶላር ወርሃዊ አማካኝ ክፍያ ህይወቱን ለመለወጥ ባለመቻሉ ስደትን አማራጭ አድርጎታል ብሎአል። የቢቢሲው ኢድ በትለር ዱከም ላይ ያናገራቸው በርካታ ስራ አጥ ወጣቶች ስደትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው እንደሚያስቡ ተናግረዋል።
ግንባታዎች እና የኢኮኖሚ እድገት ቢታይም፣ ኢትዮጵያ ከካምፖዲያና ባንግላዲሽ ባነሰ መጠን በአለም ላይ የመጨረሻውን ዝቅተኛ ክፍያ የመትከፍል አገር በመሆኗ፣ ሰራተኛው በየጊዜው እየናረ የሚሄደውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም አላስቻለውም። በኢትዮጵያ እርካሽ ጉልበት መኖሩን ያወቁት የውጭ አገር ኩባንያዎች ፣ ወደ አገሪቱ ገብተው በገፍ ምርት እያመረቱ ቢሆንም፣ የሰራተኛውን ህይወት ግን ሊለውጡለት አልቻለም ሲል ነቅፏል።
በዚህ ክፍያ ህይወትን ማቆየት እጅግ ከባድ ነው የሚለው ጋዜጠኛ በትለር፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታውን አቶ አህመድ ሸዲን፣ “ለመሆኑ አገሪቱን አማካኝ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እናሰልፋታለን ስትሉ፣ የሰውን ገቢ ስንት ብላችሁ አስባችሁ ነው?” በማለት ጠይቆታል። ሚኒስትር ዲኤታው ጥያቄውን በማድፈንፈን ሳይመልሱት ቀርተዋል።
የአለም አቀፍ የሰራተኞች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ጋይ ራይደር ፣ ኢትዮጵያውያንን ክብርን ከሚያዋርድ ድህነት መታገድ ይገባል ብለዋል።
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ እና የምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ፣ በአዲስ አበባ አብዛኛው ሰራተኛ በ900 ብር ገቢ የቤት ኪራይ ከፍሎና የምግብ ወጪውን ሸፍኖ ለመኖር እንዳልቻለ ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው አህመድ ሸዲ አገሪቱ እያደገች ስትሄድ ክፍያው እንደሚሻሻል ቢገልጹም፣ ጋዜጠኛው ለውጡ አሁን አስፈላጊ መሆኑን ወጣቶችን በማናገር ገልጿል።
ቢቢሲ ኢትዮጵያዊው ወጣት ህይወቱን ለማቆየት ሲል አገሩን ጥሎ እንደሚሰደድ በዘገባው ቢያሳይም፣ በደሃውና እና በሃብታሙ መካከል እየናረ ስለመጣው የኑሮ ልዩነት ያነሳው ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 100 ስደተኛ ኢትዮጵያውያንን የጫነ መኪና ኬንያ ውስጥ ተይዟል። ኢትዮጵያውያኑ በሞያሌ በኩል አድረገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ በመጓዝ ላይ ነበሩ። በመንገድ ላይ እየተሹለኮለኩ ለ3 ቀናት ያክል መቆየታቸውን የገለጸው ፖሊስ፣ ከፍተኛ ድካም እንደሚታይባቸውም ገልጿል። ኢትዮጵያውያኑ ወደ እስር ቤት የተወሰዱ ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።