ኢሳት ዜና (ሃምሌ 13 2007 አም)
የበክኔል ዩኒቭርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑትና በቅርቡ ከዚሁ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማእረግ የተቀበሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በሳምንቱ መጨረሻ ኤርትራ መግባታቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ አብይ መነጋገሪያ ሆኖ ወጥቷል ፤ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የመሪውን ትግል ቦታ መሄድ ይፋ በማድረግ ኢትዮጵያውያን በአቅማቸው መጠን በትግሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
“እነሆ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ድ/ር ብርሀኑ ነጋ በአካል ትግል ሜዳ ውስጥ ይገኛል የሚችል ሁሉ እንዲከተል ፤ መከተል የማይችል በያለበት ሆኖ ትግሉን እንዲያጧጡፍ አርነኞች ግንቦት ሰባት ጥሪ ያደርጋል’’ ሲል ንቅናቄው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባወጣው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።
አርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ “ሊቀመንበራችን ትግል ሜዳ ውስጥ ነው” በሚል ርእስ ሐምሌ 12/2007 ባወጣው መግለጫ “ አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ የአመራሩ በትግሉ ሜዳ ውስጥ መገኘት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ሊቀመንበሩን ጨምሮ አመራሩን ወደ ትግል ቦታ አንቀሳቅሷል፤ በዚህ መሰረት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ ወደ ትግል ሜዳ ወርደዋል’’ ያለው የንቅናቄው መግለጫ ሲቀጥልም “ወሳኝ የሆነ ትግል ውስጥ ገብተናል የትግሉ መሪዎችም የህይወት መስዋትነት የሚከፈልበት ቦታ ላይ ይገኛሉ’’ ካለ በኋላ ኢትዮጵያውያን እጅ ለእጅ ተያይዘን ዘረኛውን የህወሀት አገዛዝ ለማስወገድ በጋራ እንስራ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሊቀመንበር ዶ/ር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በትግል ሜዳ ላይ የሚገኙ የድርጅታቸውን አባላት ለመቀላቀልና በቅርብ አመራር ለመስጠት ወደ ኤርትራ መጓዛቸው በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ የደስታ ስሜት የፈጠረ ሲሆን ትግሉ የምርና ወሳኝ ደረጃ ላይ ለመድረሱ አመላካች ነው ተብሏል። የስራቱ ደጋፊዎችም በተቃውሞ አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ።