ሐምሌ ፲፬ (አስራአራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ሳምንት እንደ አዲስ ባገረሸው የምስራቅ እዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የሃረሪ ክልል ፖሊሶች ግጭት 4 ፖሊሶች በመከላከያ አባላት ታፍነው መወደሳቸውንና እስካሁን የደረሱበት አለመታወቅን የሃረር ወኪላችን ገልጿል። የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ከሁለቱ ሃይሎች የተውጣጡ መሪዎችን ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
በሃረሪ ፖሊስና በምስራቅ እዝ የፖሊስ አባላት መካከል ያለው ግጭት የቆየ ሲሆን ፣ አንድ አንድ ደም ሲፋስስ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግልግል ሲፈታ ቆይቷል። ባለፈው ሳምንት አንድ የፖሊስ ባልደረባ በህገወጥ ንግድ ሲሰመራ የያዘውን ወታደር፣ ንብረት በመቀማት ማሰሩን ተከትሎ፣ ” ለምን ተነካን” በሚል ስሜት ሌሎች የእዙ ወታደሮች መሳሪያ ታጥቀው የፖሊስ ኮሚሽን ጽ/ቤትን የወረሩ ሲሆን፣ ምሽት 12 ሰአት ከ30 አካባቢ ከተራኛ ፖሊሶች ጋር ለ2 ሰአት ያክል ተኩስ ተለዋውጠዋል። ወታደሮቹ በኮሚሽኑ ጽ/ቤት ውስጥ የሚገኙ ፖሊሶችን በማባረር፣ መስሪያ ቤቱን እስከ እሁድ ጠዋት ድረስ በቁጥጥራቸው ስራ አድርገውታል። በመካለያ ጥይት የቆሰሉ ሰዎች ቢኖሩም በቁጥር ለማወቅ አልተቻለም። በርካታ ፖሊሶችም ከጥቃቱ ለማምለጥ ሲሩዋሩዋጡ ታይቷል።
ምሽት አካባቢ የክልሉን ፕሬዚዳንት ጠባቂ በመደብደብ መሳሪያውን የቀሙ ሲሆን፣ በማግስቱ እሁድ ፕሬዚዳንቱ የፖሊስና መከላከያ ሃላፊዎችን ጠርተው ቢያነጋግሩም ለችግሩ ጊዚያዊ መፍትሄ የተገኘለት ቢመስልም፣ በወታደሮች ቁጥጥር ስር የዋሉት 4 ፖሊሶች ጉዳይ እስካሁን እልባት ባለማግኘቱ ውጥረቱ አልበረደም።
ፖሊሶቹ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በምሽት እየደበደቡን ነው፣ ከሃቅማችን በላይ ሆነዋል ብለው የፖሊስ ኮሚሽነሩ በሰበሰቡት ስብሰባ ላይ ቢያስታውቁም፣ “አትናገሩዋቸው” የሚል መልስ በማግኘታቸው፣ ጥቃት ሲድርስባቸው ራሳችን እንኳ ለመከላከል አልቻሉም።
የችግሩ አሳሳቢነት ለኢታማጆር ሹሙ ሳሞራ ኑስ ሳይቀር ሪፖርት ቢደረግም እስካሁን የተሰጠ መፍትሄ የለም። የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች የክልሉን ፖሊሶች ” ከጸረ ሰላም ሃይሎች ጋር ግንኙነት አላቸው” በሚል እየከሰሱዋቸው ሲሆን፣ የፖሊስ አባላቱ ደግሞ’ “ሰራዊቱ ለሚፈጽመው ህገወጥ ተግባርና ግፍ ማምለጫ ምክንያት ነው” በማለት ይናገራሉ። ከአሁን በፊት አንድ የፖሊስ አባል በመከላከያ ሰራዊት ከተወሰደ በሁዋላ፣ የት እንደገባ ሳይታወቅ አንድ አመት መሙላቱን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሃረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።