ሐምሌ ፲፬ (አስራአራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአርባምንጭ ምንጮች እንደገለጹት ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ፖሊስ አባላት በየአንዳንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ፍተሻ ሲያደርጉ የታየ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ላቀረቡት ጥያቄ የተሰጣቸው መልስ ” ግንቦት7″ ከተማው ውስጥ ገብቷል የሚል ነው።
በከተማውና በዙሪያ ወራዳዎች የሚታየው ፍተሻና ቁጥጥር መጨመሩን ፣ ህዝቡም ግራ ተጋብቶ እንደሚገን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የጋሞን ህዝብ አዋርደዋል በተባሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ የተጠራው ተቃውሞ በጸጥታ ሃይሎች የተጨናገፈ ሲሆን፣ የተቃውሞ ሰልፉን ለማድረግ የወጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተይዘው ታስረዋል። አብዛኞቹ እስከ ትናንት መለቀቃቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሌላ ዜና ደግሞ የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ትግሉን መሬት ላይ ወርደው ለመምራት አስመራ መግባታቸውን በተመለከተ የተለያዩ ወገኖች አስተያየታቸውን እያቀረቡ ነው።
አንድ አስተያየት ሰጪ ” እርሳቸው ተደላድለው መኖር ሲገባቸው፣ የአገር ጉዳይ ነው ብለው ወርደዋል። ወጣቱ ትግሉን ለመቀላቀል ዝግጁ ነው” ብለዋል””
ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ” ከተማና ገጠሩ እየተነገጋረበት መሆኑን አስታውሰው፣ ከፍተኛ መነቃቃት መፈጠሩንና ሌሎችንም የሚያነሳሳ መሆኑን” ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ አርበኞች ግንቦት7ትን ለመቀላቀል ሲሄዱ መንገድ ላይ የተያዙት ቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች በውሳኔያቸው እንደማይጸጸቱ ገለጹ። ወጣት እየሩሳሌም ተስፋው ከቃሊቲ፣ ብርሃኑ ተክለያሬድና ፍቅረማርያም አስማማው ከቂሊንጦ እስር ቤት በጋራ በጻፉት ደብዳቤ ” በሰላማዊ ትግል ጓዶቻችን የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና፣ መልካም ህልም አላሚዎቹ የዞን ፱ ጦማርያን ያለምንም ወንጀል ወደ ማጎሪያ ቤት በተወረወሩ ጊዜ ”የሀገራችን እጣ ፋንታ ምንድነው?ትግሉስ ከኛ ምን ይፈልጋል?” የሚሉ የወቅቱን ወሳኝ ጥያቄዎች በማንሳት ስድስት ወራት ከፈጀ ሰፊ ውይይት በኋላ ምርጫችን ሁሉን አቀፍ ትግል መርጦ ለሀገር ነጻነት በሚታገለው፣ሀገራችንን ከፋሽስታዊው አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ሌት ተቀን ሞትን ተጋፍጠው የሚተጉ አባላትና ትግሉን ስኬታማ ለማድረግ በልበ ሙሉነት ለስልጣን ሳይሆን ለሞት የሚሽቀዳደሙ መሪዎች ወደ ተሰባሰቡበት፣በአገዛዙ ፓርላማ ሽብርተኛ የሚል የዳቦ ስም ወደተሰጠው ግንቦት 7 ወደተሰኘው ነጻ አውጪ ድርጅት ማድረጋችን፣ መቼም የማንጸጸትበት ሁሌም በኩራት ደጋግመን የምንናገረው ምርጫ” ነው ብለዋል።
“በስርዓቱ ጠባቂዎች እጅ መውደቃችን ውሳኔያችንን በድጋሜ እንድንመረምር አላደረገንም” ያሉት ወጣቶቹ፣ “ዛሬም በአቋማችን ጽኑ ነን! ዛሬም የኢትዮጵያውያን ነጻ አውጭ ድርጅት የሆነው የግንቦት 7 አባላት ነን! ይህንንም በኩራትና በልበ ሙሉነት ለማዕከላዊ ደብዳቢዎች /መርማሪዎች/ አስረድተናቸዋል፡፡” ብለዋል።
ለማህበራዊ ሚዲያ በበተኑት ደብዳቤ ፣ የግንቦት7 አባላት ነን ብለን በድፍረት ለመርማሪዎች በመናገራችን ” ደብዳቢዎቻችንን አበሳጭቶ ፣ ሴትን ልጅ ራቁቷን አቁሞ ከሚደረግ የጭካኔ ምርመራ አንስቶ ዓይንን ታስሮ ውሃ እየደፉ እስከ መደብደብ የደረሰ ግፍ በደብዳቢዎቹ መሪ ኮማንደር ተክላይ ጭምር ተፈጽሞብናል፡፡” ብለዋል። ” በምርመራው መሐልም ግንቦት 7 አሸባሪ ድርጅት ነው ብለን እንድንናገር፣ ወደ ትግሉ የገባነው አሜሪካ ባሉ የድርጅቱ አመራሮች ተታልለን ነው እንድንል ፣ ሀገር ውስጥ ፍጹም ሰላማዊ ትግል ማድረግን የመረጡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችን ከግንቦት 7 ጋር ይገናኛሉ እንድንል ” ተነግሮን ነበር ሲሉ አጋልጠዋል።
“የአንዳችንን ስቃይ በአንዳችን በማስፈራራት ‹‹እሱን ከምንደበድበው፣ እሷን ራቁቷን ከማቆማት እመን/እመኝ” የሚለው ማስፈራሪያ” እንደነበር የገለጹት ወጣቶቹ፣ ሆኖም ” በቃላችን ጸንተን አካላችን እንጂ መንፈሳችን ሳይጎዳ የተለመደውን የሽብርተኝነት ክስ ተጎናጽፈን ወደ ቃሊቲና ቂሊንጦ ማጎሪያ ቤቶች ተዛውረናል” ብለዋል።
በሰላማዊ ትግል የአጭር ጊዜ ቆይታቸው ብርሃኑ ተ/ያሬድ ለ19 ጊዜያት፣ ፍቅረማርያም አስማማው ለ9 ጊዜ፣ እየሩሳሌም ተስፋው ለ7 ጊዜ በአገዛዙ እስር ቤቶች በግፍ ለእስር መዳረጋቸውን ገለጸዋል፡፡
“እጃችን ቢታሰርም መንፈሳችንን ሊያስሩት አይችሉም” ያሉት ወጣቶቹ፣ “ዛሬም የጀግኖች አንበሶቻችን የድል ጩኸት በጆሯችን ይሰማናል፡፡ የበሰበሰውን ዛፍ ለመጣል የተዘረጋው የአንበሶች ክንድ ይታየናል፡፡ ይህ ክንድ የበሰበሰውን ዛፍ ሳይጥል አይሰበሰብም፡፡ በብስባሹ ውድቀት ውስጥም ዴሞክራሲ ያብባል፣ ፍትሃዊነት ይነግሳል፣ እኩልነት ይሰፍናል፡፡ ይህ በወኔ እስር ቤት ያሉ ወጣቶች የቀቢጸ ተስፋ ህልም አይደለም፡፡ ተደጋግሞ በታሪክ የታየ አሁንም በቅርብ የሚፈጸም እውነት እንጂ!!” ሲሉ ደብዳቤያቸውን ቋጭተዋል።
ብርሃኑ ተክለያሬድ የሰማያዊ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ነበረ ሲሆን፣ እየሩሳሌም እና ፍቅረማርያም ደግሞ የምክር ቤት አባላት ነበሩ። ሶስቱም ወጣቶች በሰላማዊ ትግል ከፍተኛ መስዋትነት ከከፈሉ በሁዋላ፣ ይህ መስመር አያዋጣንም ብለው ወደ ኤርትራ ሲሄዱ ማይካድራ በተባለ ስፍራ ላይ ተይዘዋል። ወጣቶቹ ጉዞዋቸውን ከማድረጋቸው በፊት ውሳኔያቸው ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እንዳይያዝ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን እንዲሁም ውሳኔው የራሳቸው ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ስለ ሶስቱ አባሎች ተጠይቀው ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ መናገር እንደማይፈልጉ፣ ይሁን እንጅ አሁን ያለው አፈና ወጣቱ የትጥቅ ትግሉን መንገድ ቢከተል እንደማያስገርም መናገራቸው ተዘግቧል።
የእነ ብርሃኑ ደብዳቤ ታጋይ አበበ ካሴ ከቃሊቲ እስር ቤት የደረሰበትን ግፍ እና ለትግል ያለውን ጽናት በገለጸ ማግስት የወጣ ሲሆን፣ ወጣቶቹ በድፍረት የጻፉት ጽሁፍ በማህበራዊ የመገናኛ መድረክ ከፍተኛ ሽፋን ተሰጥቶታል።