የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጠበቃ የሆኑት ለደንበኞቻቸው ያቀረቡት መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደረገ

ሐምሌ ፲፬ (አስራአራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ከ1 እስከ 6ኛ እንዲሁም የ9ኛ ተከሳሽ ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ በደንበኞቻቸው ላይ በቀረበባቸው የክስ ማስረጃ ላይ ያቀረቡት ባለ 10 ገፅ መቃወሚያ በፍርድ ቤቱ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ተደርጓል፡፡ ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ ተከሳሾቹ ሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም ተይዘው ከሶስት ወር በኋላ ጥቅምት 7 ቀን 2006 ዓ.ም ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ተገኘ የተባለ መረጃ ከአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ማስረጃ ዝርዝርነት እንዲወጣ፣ተከሳሾቹ ለፖሊስ መረጃ የሰጡበት መንገድና ፖሊስ የሰነድ ማስረጃዎችን የያዘበትን መንገድም አቃቤ ህግ ህጋዊ መሆኑን ስላላረጋገጠ በደንበኞቼ ላይ በማስረጃነት እንዳይያዝ ሲሉ መቀወወሚያ አቅርበው ነበር፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል በዛሬው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ ዘላለም ወርቃገኘሁ ‹‹መቃወሚያው የቀረበው ከተከሳሾች እጅ ተገኙ የተባሉት ማስረጃዎች በህጋዊ መንገድ የተገኙ ስለመሆናቸው አቃቤ ህግ በማስረጃ ስላላረጋገጠ ነው›› ሲል ፍርድ ቤቱ መቃወሚያውን እንዲቀበለው ጠይቋል፡፡ሆኖም ዛሬ ሀምሌ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መቃወሚያውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርጎታል፡፡በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በነፃ ይሰናበቱ ወይንም ይከራከሩ የሚለውን ለመወሰን ለብይን ለነሀሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዚህ መዝገብ ተከሰው አቶ ተማም መቃወሚያ ካቀረቡላቸው መካከል አቶ የሸዋስ አሰፋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤል ሺበሽ ይገኙበታል፡፡
በዘላለም ወርቅአገኘሁ የክስ መዝገብ ከ1 እስከ 6ኛ እንዲሁም 9ኛ ተከሳሾች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጉ ከጥብቅና በመታገዳቸው ምክንያት ሰባቱም ተከሳሾች በዛሬው ችሎት ያለ ጠበቃቸው ቀርበዋል ሲል ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
በሌላ ዜና ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ መኳንንት ብርሃኑ የካ ክፍለ ከተማ ኮተቤ አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፌደራል ፖሊስ ተከቦ እየታደኑ ሲሆን ፣ አቶ መኳንንት ለሳምንት ያህል ቤታቸው እንዳልገቡ ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል፡፡ፖሊስ አቶ መኳንንትን የሚያድንበትን ምክንያት ለጊዜው ማወቅ እንዳልተቻለ ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ከዚሁ ከእስር ዜና ሳንወጣ ፣ በአቶ አበባው መሃሪ የሚመራው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከምርጫ 2007 በሁዋላ ከ132 አባሎች በላይ በግፍ በእስር ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ገዥው ፓርቲ የታሰሩ አባሎቹን በአስቸኳይ እንዲፈታና ከመሰል ድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቋል
መኢአድ በዛሬው ዕለት በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገዥው ፓርቲ ራሱ ላወጣው ሕግ እንኩዋን ተገዥ ባለመሆን ምርጫው ተሳትፎ የነበራቸውን የፓርቲውን አባላት በየክልሉ አሳድዶ በማሰርና ማንገላታት ስራዬ ብሎ ተያይዞታል ሲል ክስ አቅርቦአል፡፡ በሀገሪቱ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰበት ሄዶአል ያለው ፓርቲው፣ ያለምንም ምክንያት አባሎቻችንን ወህኒ ቤት በመወርወር በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው ሲል አክሏል፡፡
አባሎቻችን የታሰሩት በያዙት የፖለቲካ አመለካከት ምክንያት ነው ያለው ፓርቲው፣ እነዚህኑ ወንድሞቻችንን ለማሰብ በየወሩ
የሻማ ማብራት ስነስርኣት ለማካሄድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ከ2007 ምርጫ በሁሃላ የመድረክ አምስት አባላት በትግራይ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች፣ የሰማያዊ ፓርቲ አንድ አባል ደግሞ በደብረማርቆስ ሲገደሉ በርካታ አባሎች ለእስር ተዳርገዋል።