ሰኔ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ የሰማያዊ ፓርቲ የምስራቅ ጎጃም አደራጅ የሆነውን የወጣት ሳሙኤል አወቀን ገዳይ በ19 አመታት እንዲቀጣ ውሳኔ አስተላልፎበታል። ይሁን እንጅ ገዳይ ተብሎ የቀረበው አቶ ተቀበል ገዱ ለፍርድ ቤት የሰጠው ቃል እና ፖሊስ በወቅቱ የሰጠው መግለጫ ሊጣጣሙ አልቻሉም። ገዳይ ተብሎ የቀረበው ሰው ለፍርድ ቤቱ ግድያውን የፈጸመው መጠጥ ቤት አብረው ካመሹ በሁዋላ መሆኑን ሲናገር፣ ፖሊስ በበኩሉ ገዳይ ” ድርጊቱን የፈፀመው ከመሬት ጋር በተያያዘ በነበረ ክርክር፣ ገዳይ ክርክሩን በመረታቱ ተባሳጭቶ ነው የሚል ” መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን ሰጥቶ ነበር። ገዳይ በድጋሜ ሲጠየቅ ድርጊቱን የፈጸመው ” ከሌላ ሰው ገንዘብ ተቀብሎ መሆኑን የተናገረ ሲሆን፣ አብሮት አለ የተባለውን ሰው ማንነት ግን ሊገልጽ አልቻለም። ፖሊስ ደግሞ ድርጊቲ በጨለማ የተፈጸመ በመሆኑ የአንደኛውን ሰው ማንነት ለማወቅና ለመያዝ አለመቻሉን ገልጿል።
ፖሊስ የሰጠው ቃልና ገዳይ የሚናገረው አንድ አለመሆን፣ መንግስት ጉዳዩን ሆን ብሎ ለመሸፋፈን የሄደበት ጥረት አለመሳካቱን እንደሚያሳይ የሟች ቅርብ ጓደኞች ለኢሳት ገልጸዋል። አንዳንድ ነገሮች ልሸፈን ቢሉ አይሸፈኑም፣ የሳሙኤል አሟሟትም ሊሸፈኑ ከማይችሉ ሃቆች መካካል አንዱ ነው ይላሉ ጓደኞቹ።
“ሁለተኛው ግለሰብ አለመያዙ፣ ፖሊስ ማንነቱን ለማወቅ አልቻልኩም” ማለቱ በራሱ ከግድያው ጀርባ ያለውን አንድ ሃይል እንደሚያሳይ እነዚሁ ሰዎች ይገልጻሉ።
ሳሙኤል ከመሞቱ በፊት፣ የአካባቢው ሹሞች እንደሚገድሉት እየዛቱበት መሆኑን ገልጾ ነበር። “እኔ ብሞትም ለነጻነት የሚደረገው ትግል እንዳይቆም” ሲል ለወጣቱ አደራ መልእክት ትቶ ማለፉ መዘገቡ ይታወቃል።