ሰኔ ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን በአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን በድንገት በተጠራው ስብሰባ ኮሚሽነር ያየህ አዲስ ፣ የብሄራዊ ሊጉ ጨዋታዎች በሚካሄዱበት ከተሞች ከምርጫ 2007 በኋላ የሚታዩ የስፖርታዊ “ጨዋነት ጉድለቶች” አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ወቅቱ የምርጫ ውጤት ይፋ የሆነበት በመሆኑ በተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎች ላይ ልዩ ጥንቃቄ እንዲደረግም ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ያየህ ” ዛሬ በስፖርት ሜዳ የሚታየው ተቃውሞ በጥቃቅን ነገሮች እንደሚነሳ ተናግረው፣ ጥቂት አጥፊዎችን መቆጣጠር ባለመቻላችን ፣ በባህርዳር ላይ የተካሄደውን የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ተከትሎ በሌላ ክልል የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ጫፍ እስከ ጫፍ መፈናቀላቸውን አስታውሰዋል። በድሬዳዋ በሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ስጋት ያላቸው መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ ከወዲሁ ራስን ለመከላከል ዝግጅት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለመነጋገር በአጣብቂኝ ውስጥ ሆነው አስቸኳይ ስብሰባ መጥራታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ያለንበት ወቅት የዲሲፕሊን ዝንፈት አይፈልግም ያሉት ኮሚሽነር ያየህ፣ በምክንያት ያስቀመጡትም ህዝቡ ትልቅ ምርጫ ያካሄደበት ማግስት መሆኑን ነው። ከምርጫው በሁዋላ በአማራ ክልል በ5 ቦታዎች ላይ የጥይት እሩምታ ነበር ያሉት ኮሚሽነሩ መኪኖች ተሰብረዋል፣ የግለሰቦች ቤት ተደብድቧል፣ ሰላማዊ ሰዎች ተመተዋል ብለዋል። በደብረወርቅ፣ አይከል፣ በዳባት እንዲሁም በባህርዳር ሰላማዊ የሚመስል የውስጥ ለውስጥ ተቃውሞዎች የታዩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በደብረማርቆስ ደግሞ ባለፉት 2 ሳምንታት በተካሄደው የስፖርት ጨዋታ ምንነቱን ባልታወቀ ምክንያት የስፖርት ሜዳዎች ጭር ማለታቸውን ገልጸው፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ሃገሪቱን የሚመሩ የከተማዋ ባለስልጣናት ሳይቀር ሜዳ ውስጥ ከፖሊስ ጋር ግጭት መፍጠራቸው ጉዳዩ ሌላ መልክ እየያዘ መሄዱ አሳሳቢ እንደሆነና ፣ ”ይህንን እንቅስቃሴ ማነው የሚያነሳሳው ?” የሚለውን ለመመለስ እንደተሳናቸው በመናገር ‘ችግሩ ቀጣይነት ሊኖረው ይችላል ‘ ብለዋል
በሌላ በኩል ዘንድሮ በተካሄደው የሊጉ ጨዋታ የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ምንም ድጋፍ እንዳላደረገላቸው የገለጹት ተሳታፊ “ዛሬ ስልካችን ከየት አግኝታችሁ ደወላችሁ?” በማለት በግርምት ሲጠይቁ ተሰምተዋል፡፡የኮሚሺኑ ጽህፈት ቤት ጨዋታውን አይከታተልም ትክክለኛ ውጤት ለሚዲያ አይገልጽም በማለትም ተችተዋል፡፡