በቴፒ የወረዳው አዛዥና ፖሊሶች ታሰሩ

ሰኔ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ ለመብት የሚታገሉ የከተማዋ ወጣቶች በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ የፌደራል ፖሊስና የጸረ ሽብር ግበረሃይል አባላት በከተማዋ ተገኝተው እጃቸው አለበት
ብለው የጠረጠሩዋቸውን የቴፒ ወረዳ አስተዳዳሪን ጨምሮ 7 ፖሊሶችን ይዘው አስረዋል።
ባለስልጣኖቹ የከተማውን ህዝብ ያነጋገሩ ሲሆን፣ ህዝቡ በነጻነት እጦት እየተሰቃየ መሆኑንና ወጣቶች እርምጃ የሚወስዱት ከዚህ ተነስተው መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በአካባቢው የሚታየውን ችግር አጣሩ ተብለው ወደ አካባቢው የሚላኩት የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት፣ ከወረዳ ባለስልጣናት ጉቦ እየተቀበሉ ችግሩን ሲያድበሰብሱ ቢቆዩም፣ አሁን ግን ችግሩን መሸፈን በማይቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን ለመላክ መገደዱን ምንጮች ገልጸዋል።
ከወር በፊት እንድሪስ ቀበሌ ላይ የመንግስት ታጣቂዎች 5 ንፁሀን ዜጎችን ከገደሉ በሁዋላ፣ ታጣቂዎች በወሰዱት እርምጃ 3 ፖሊሶችና ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ወታደሮች ሙት እና ቁስለኛ ሲሆኑ፣ ከታጣቂዎች ወገን ደግሞ 2ቱ ተገድለዋል።
ታጣቂዎችን ለመያዝ የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላት እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም እስካሁን አልተሳካላቸውም።