የኢኮኖሚው መሰረት ነው የተባለው የውጭ ንግድ መክሸፉን ሚኒስትሩ በይፋ ተናገሩ

ሰኔ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት ከአምስት አመት በፊት አውጥቶት በነበረው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከወጪ ንግድ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚሰበስብ ገልጾ ነበር፣ ይሁን የገንዘብ ሚኒስትሩ ዛሬ ይፋ እንዳደረጉት የታቀደው
እቅድ አለመሳካት ብቻ ሳይሆን የውጭ ንግዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መሄዱን ገልጸዋል።
አቶ ሱፊያን አህመድ የ2008 በጀት ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በውጭ ንግድ የትራንስፎሜሽን እቅዱ አልተሳካም ብለዋል።
በ2003 በጀት ዓመት የውጭ ንግድ አፈጻጸም ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ 17 በመቶ የነበረ ሲሆን ይህ አሃዝ በ2006 ዓ.ም ወደ 11. 7 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡
የውጭ ንግዱ እያሽቆለቆለ በመጣበት በዚህ ወቅት የገቢ ንግዱ መጨመር ሚዛኑን በከፍተኛ ደረጃ እንዳዛባው ታውቋል፡፡ በ2006 በጀት ዓመት የውጭ ንግዱ ከአጠቃላይ አገር ውስጥ ምርት 11. 7 በመቶ ሲመዘገብ የገቢ ንግዱ ግን 29. 5
በመቶ ተመዝግቦአል፡፡ በዚህም ምክንያት የውጭ ንግዱ አፈጻጸም እያሽቆለቆለ መመጣት እና የገቢ ንግዱ መጨመር የንግድ ሚዛኑ ጉድለት እየሰፋ እንዲሄድ አድርጎታል።
አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚሉትየውጭ ንግዱ እየተዳከመ መምጣቱ በአገሪቱ ውስጥ እየተባባሰ ለመጣው የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
መንግስት ለሚቀጥሉት አምስት አመታት አዲስ የ5 አመት እቅድ መንደፉን ቢገልጽም፣ እቅዱን እስካሁን ለህዝብ ይፋ አላዳረገም። በመንግስት በኩል ከሚለቀቁ መረጃዎች ለመረዳት እንደሚቻለው በአዲሱ የአምስት አመት እቅድ የምግብ ዋስትናን
ማረጋገጥ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል ተካቷል። በሌላ ዜና ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በኢትዮጵያ የተረጅዎች ቁጥር መጨመሩን አስታውቋል። ከየካቲት እስከ ግንቦት ባሉት ወራት በበልግ አብቃይ ቦታዎች በቂ ዝናብ
ባለመዝነቡ በተወሰኑ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የምግብ ዋስትና ችግር ተከስቷል። በሶማሊ ክልል በፈረንጆች አቆጣጠር ከ ሰኔ 8 ጀምሮ በተቀሩት የአገሪቱ ክፍሎች ደግሞ ከሰኔ 22 ጀምሮ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልገው ህዝብ ቁጥር
በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
እስካሁን ድረስ ከአፋር፣ አማራ፣ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች የነፍስ አድን የእርዳታ ጥሪ መቅረቡን ድርጅቱ ገልጿል። ከፍተኛ የሆነ የምግብ እጥረት ባጋጠማቸው ወረዳዎች የሚዝል በሽታን ስርጭት መቆጣጠር እንደሚያስፈልግም ድርጅቱ አክሎ
ገልጿል።
ምእራባውያን መንግስታትና አለም ባንክ አሁንም ከ8 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ያደርጋሉ። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያቀረበው ሪፖርት እነዚህን በምግብ ለስራ የተካተቱ ዜጎችን አይጨምርም።