ኤርትራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ሪፖርት አጣጣለችው

ሰኔ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በኤርትራ ይፈጸማሉ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ይፋ እንደሚያደርግ ካስታወቀ በሁዋላ፣ ኤርትራ መልስ ሰጥታለች።
የድርጀቱ ሪፖርት በሃሰት የተሞላና ነው ያለው የኤርትራ መንግስት መግለጫ፣ ድርጅቱ ጥቃቱን የሰነዘረው በመንግስት ላይ ሳይሆን ለሰው ልጅ ክብርና ማንነት ከፍተኛ ከበሬታ በሚሰጠው ስልጡን በሆነው ማህበረሰብና ህዝብ ላይ ነው ብሎአል።
የኤርትራ መንግስት “የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት ለሰብአዊ መብቶች ከበሬታ የምትሰጠውን አገር ለማንበርከክ ከሚደረጉት ዘመቻዎች መካከል አንዱ ነው” ሲል ሪፖርቱን ተቃውሟል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ ካቀረባቸው ወንጀሎች መካከል የዘፈቀደ ግድያ፣ ስደትና ብሄራዊ ውትድርና የሚሉት ይገኙበታል። የኤርትራ መንግስት በምእራባውያን መንግስታት ለሚቀርብበት ውንጀላ አብዛኛውን ጊዜ መልስ አይሰጥም።