ግንቦት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጋምቤላና ደቡብ ክልል አዋሳኝ ከተማ በሆነቸው ቴፔ ትናንት ሌሊት 11 ሰአት ላይ ለተሻለ ፍትህና ነጻናት እንታገላለን የሚሉ ታጣቂዎች በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ በወሰዱት
እርምጃ 3 የሌሊት ተረኛ ፖሊሶች ሲገደሉ በርካታ እስረኞችንም አስፈትተዋል።
ቁጥራቸው ከ100 እስከ 150 የሚሆኑ በቴፒና አካባቢው የሚታየውን ዘረኝነትና የአስተዳደር በደል እንዋጋለን በማለት ራሳቸውን አደራጅተው ጫካ የገቡ ወጣቶች ባለፉት 9 ወራት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ቢቆዩም ትናንት ሌሊት
የፈጸሙት ጥቃት ከእስካሁኑ የተለየ ነው ተብሎአል።
የፖሊስ ጣቢያው በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አቅራቢያ የሚገኝ ሲሆን በአካባቢውም የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ሰፍረው በአካባቢው ተደጋጋሚ ቅኝት ያደርጋሉ። ታጣቂዎቹ ከአንድ ቀን በፊት ለፖሊስ አባላት
ጥቃት እንደሚፈጽሙ ማስጠንቀቂያ የላኩ ሲሆን፣ በቃላቸው መሰረት ሌሊት ላይ ፖሊስ ጣቢያውን ሰብረው በመግባት በጣቢያው ውስጥ ተከማችተው የሚገኙትን የጦር መሳሪያዎች እስከ እነ ጥይቶቻቸው እንዲሁም የተለያዩ ሰነዶችን
ሰብስበው ወስደዋል። በሶስት ክፍል ታስረው የነበሩ እስረኞችን ሲለቁ፣ የራሳቸውን አባላት ይዘው ጠፍተዋል።
ተረኛ ፖሊሶች ተኩስ የከፈቱ ቢሆንም ታጣዊዎች በወሰዱት እርምጃ አንድ መቶ አለቃ ማእረግ ያለው ፖሊስና ሁለት ተራ ፖሊሶች ተገድለዋል። አንድ የባጃጅ ሹፌር የሆነ እስረኛም በተኩሱ ማሃል ህይወቱ አልፎአል። የመንግስት
ወታደሮች ተከታትለው ጥቃት ለመፈጸም ባደረጉት ሙከራ ለታጣቂዎቹ መረጃ በማቀበል ሲተባበር የነበረን አንድ ሰው ገድለዋል። ሟቹ የሚቀብረው አጥቶ ጫካ ላይ ተጥሎ እስከ እኩለቀን መታየቱን የአይን ምስክሮች ተናግረዋል።
ታጣቂዎች የአካባቢው ህዝብ ድጋፍ እንዳላቸውም ነዋሪዎች ይናገራሉ። አንዳንድ ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ታጣቀዊዎች በወሰዱት እርምጃ የከተማው ህዝብ ደስታውን ሲገልጽ ታይቷል ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በቴፒ ከተማ እንድሪስ ቀበሌ ውስጥ 5 ሰዎች ከሌሊቱ 8 ሰአት ላይ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። በወቅቱ ከተገደሉት መካከል አባትና ልጅ ይገኙበታል። ግድያውን የፈጸሙት ፖሊሶች ሲሆኑ፣ ማቾቹ
በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን ይደግፋሉ በሚል ምክንያት መገደላቸውን ኢሳት በወቅቱ ዘግቦ ነበር።
ካለፈው ከመስከረም ወር ጀምሮ በቴፒና አካባቢዋ ያለው ግጭት ተባብሶ በመቀጠሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውንም፣ በእየለቱ በከተማዋ ውስጥ የጥይት ድምጽ እንደሚሰማና በርካታ ቁጥር ያላቸው የሸኮ መዠንገር ነዋሪዎች
እየፈለሱ ወደ ቴፒ ከተማ በመግባት ላይ መሆናቸውን መዘገቡ ይታወሳል። የዞኑን ባለስልጣናት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ ከሰአት በሁዋላ ቴፒ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ፃኑ በተባለች ቀበሌ የመንግስት ሀይሎችና ታጣቂ ቡድኑ ባደረጉት ዉጊያ በርካታ የልዩ ሀይል ፖሊሶች ሲገደሉ በርካቶች ቆስለዉ አማን ሆስፒታል ገብተዋል ።
እስካሁን በደረሰን መረጃ 3 የአማፂያኑ አባላት ተገድለዋል::