የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪዎች በአዲስ አበባ ውይይት ጀመሩ

ሰኔ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሁለት አመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የደቡብ ሱዳን ግጭት ከዛሬ ነገ መፍትሄ ይፈለግለታል ቢባልም እስካሁን ጦርነቱን የሚያስቆም መፍትሄ ሊገኝ አልቻለም። በቀድሞው የውጭ ጉዳይ
ሚኒስትር ስዩም መስፍን ዋና መሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድር ለወራት ከተቋረጠ በሁዋላ እንደገና ለማስጀመር የሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች ተወካዮች አዲስ አበባ ገብተዋል።
ቀድም ብሎ በተቀመጠው እቅድ መሰረት የፊታችን ሃምሌ ወር በጁባ የሽግግር መንግስት የሚመሰረት ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ጦርነት እንዲሁም ሁለቱ ሃይሎች ያላቸው የሃሳብ ልዩነት ስፋት ሲታይ የሽግግር መንግስቱ እውን
ይሆናል የሚለውን ተስፋ አሟጦታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሁለቱም ሃይሎች ችግሮቻቸውን በቶሎ እንዲፈቱ ለማስገደድ ማእቀብ ቢጥልም እስካሁን የተፈለገው ውጤት ሊመጣ አልቻለም።
የደቡብ ሱዳን አማጽያን ዩኒቲ እየተባለ በሚጠራው ግዛት የሚገኙ የነዳጅ ማውጫ ጉድጓዶችን ከመንግስት ጦር አስለቅቀው መቆጣጠራቸውን ይፋ አድርገዋል። ባለፉት 2 አመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ደብዩብ ሱዳናውያን በጦርነቱ ህይወታቸውን
ሲያጡ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በጋምቤላ ክልል ከ300 ሺ ያላነሱ ደቡብ ሱዳናውያን ሰፍረው እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ።