ግንቦት ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ላለፉት 3 ሳምንታት በአውስትራሊና ኒውዚላንድ የተለያዩ ከተሞች የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ በማድረግ ላይ የሚገኘው አርበኞች ግንቦት 7 ባለፈው ዕሁድ ሜይ 31ቀን በሜልበርን
ከተማ የተሳካ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅት ማካሄዱን ሃና ጋረደው ከስፍራው ከላከችልን ሪፖርት ለመረዳት ተችሎአል
በርካታ የሜልበርንና አካባቢዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በዚህ ታላቅ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄን በመወከል የንቅናቄው የውጭ አመራር ሰብሳቢ አቶ አበበ ቦጋለ አገራችንንና ህዝቧን ህልውና ለከፍተኛ አደጋ
የዳረገው የህወሃት አገዛዝ በተባበረ ትግል የማስወገድ አስፈላጊነት ዙሪያ ድርጅታቸው ምን አይነት እንቅስቃሴ እያካሄደ እንደሚገኝ በስፋት በማብራራት ከዝግጅቱ ተሳታፊዎች ለቀረቡ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል;;
አርበኞች ግንቦት 7 በመልበርን ከተማ ባዘጋጀው የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ለረጂም ጊዜ ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ በኢትዮጵያ ላይ ያለውን አገር የማፍረስ ድብቅ ሴራ በድፍረት ሲያጋልጡ የኖሩት የቀድሞ የህወሃት መሥራችና
መሪ አቶ ገብረመድህን አረዓያ በክብር እንግድነት ተገኝተው ከተሰብሳቢው ጋር ከመወያየታቸውም በላይ በመልበርን አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የተዘጋጀላጀውን ልዩ የክብር ስጦታ መቀበላቸው ለማወቅ ተችሎአል።
አርበኞች ግንቦት7 ላለፉት 3 ሳምንታት በአደላይድ፡ በብርስበን ፡ በፔርዝና በኦክላን ኒውዚላንድ ባደረጋቸው ተመሳሳይ የገንዘብ ማሰባሰብ ዝግጅቶች ላይ ከተገኙ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር ባደረጋቸው ሰፊ ውይይቶች በርካታ ሰዎች
ድርጅቱን ለመቀላቀል የአባልነት ማመልከቻ መሙላታቸውን የገለጸው ዘገባ ፊታችን ቅዳሜ ጁን 6 ቀን ስዲኒ ከተማ በሚደረገው ተመሳሳይ ዝግጅት አውስትራሊያ ውስጥ እያደረገ ያለውን ዘመቻ እንደሚያጠናቅቅ ይጠበቃል;;