ተጨማሪ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይል ወደ ሶማሌ ክልል መሰማራቱ ተገለጸ

ኢሳት ዜና (ግንቦት 25, 2007)

በኢትዮጵያና ጎረቤት ሶማሊያ ድንበር አካባቢ የተቀሰቀሰዉን ግጭት ተከትሎ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ወታደራዊ ሃይል ወደስፍራው ማሰማራቷ ተገለፀ።

በእስካሁኑ የኢትዮጵያ ልዩ ሃይሎችና በሶማሊያ የጎሳ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደዉ ግጭት በትንሹ ከ50 በላይ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ የሶማሊያ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅመዋል ሲሉ ተቃዉሞ ማሰማታቸውን ሶማሊ ከረትን የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።

የጋልጋይዱድ ክልል ሃላፊ የሆኑት ሁሴን አርፎ የኢትዮጵያ ወታደሮች የፈፀሙትን ጥቃት ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቀያቸዉ መፈናቀላቸዉንና በአስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ መሆናቸዉን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ልዩ ሃይል እየተባሉ የሚጠሩት የፀጥታ ሃይል አባላት የወሰዱት እርምጃ የዘር ማጥፋት ድርጊት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የክልሉ ሃላፊ አክልዉ ገልጸዋል።

በአካባቢዉ ዉጥረት አለመርገቡን የሚናገሩት ነዋሪዎች በበኩላቸዉ ተጨማሪ የኢትዮጵያ የፀጥታ ሃይሎች በድንበሩ ዙሪያ መሰማራቱን ተናግረዋል። በድንበር ዙሪያ በመካሄድ ላይ ያለዉን ግጭት ተከትሎም የሶማሊያ ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ምክክር በማድረግ ላይ መሆናቸዉን ሶማሊ ከረንት ጋዜጣ በዘገባዉ አመልክቷል።

ከሳምንት በፊት በኢትዮጵያ የተካሄደዉን ምርጫ ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያ ሰራዊቷን ወደ ሶማሊያ ድንበር አስጠግታ መሰንበቷ ይነገራል።

ሃገሪቱ የወሰደችዉ እርምጃም የድንበር ግጭቱ እንዲቀሰቀስ ማድረጉን የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ናቸዉ። የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጠዉ ምላሽ የለም።