ከኬንያ ተጠልፈው የነበሩት ሁለቱ የኦብነግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ ናይሮቢ ተመለሱ

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከአንድ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የደህንነት ሃይሎች ከኬንያ ተጠልፈው ወደ ኢትዮጵያ ተወስደው የነበሩት አቶ ሱሉብ አብዲ አህመድና አቶ አሊ አህመድ ሁሴን ትናንት ምሽት
ኬንያ ናይኖቢ መግባታቸውን ለኢሳት ደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች በምን ሁኔታ ወደ ናይኖቢ እንደተመለሱ የታወቀ ነገር የለም። የድርጅቱ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አብድረህማን ሼህ ማህዲ የመሪዎቹን ወደ ናይሮቢ መመለስ አረጋግጠው፣ በምን ሁኔታ እንደተመለሱ ግን ድርጅቱ
መግለጫ እንደሚሰጥ ለኢሳት ተናግረዋል።
በኦጋዴን ነጻ አውጭ ድርጅትና በኢህአዴግ መካከል ድርድር እየተካሄደ ነው ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፣ ከዚህ በፊት አንዳንድ የድርድር ሙከራዎች ቢደረጉም፣ በአሁኑ ሰአት የሚደረግ ምንም አይነት ድርድር የለም ብለዋል።
የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አማካሪ አብዲኑር አብዱላሂ ፋራህ የኦብነግ መሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል እጃቸውን ለመንግስት መስጠታቸውን ገልጸው ነበር።
በሌላ ዜና ደግሞ ባለፉት 5 ቀናት በኢህአዴግ ወታደሮች የሚደገፉት የሶማሊ ክልል ልዩ ሚሊሺያ አባላት በኢትዮ- ሶማሊ ድንበር አካባቢ በሚኖሩ አርብቶ አደሮች ላይ በወሰዱት እርምጃ የሟችና ቁስለኞች ቁጥር ማሻቀቡን የደረሰን መረጃ
ያመለክታል።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ 35 ሲቪሎች መገደላቸውን ቢዘግብም፣ የኢሳት ምንጮች ግን የሟቾቹን ቁጥር ከ70 በላይ ያደርሱታል። በርካታ ቁስለኞች ህክምና እንዳያገኙ በኢህአዴግ ወታደሮች በመከልከላቸው ለከፋ ችግር መጋለጣቸውንም
የደረሰን ዜና ያመለክታል። ግጭቱ መዋጮ ከመሰብሰብ ጋር ተያይዞ መነሳቱን ኦብነግ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከቀናት የተኩስ ልውውጥ በሁዋላ በደቡብ ክልል በሃመር ወረዳ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በርካታ አርብቶ አደሮች በመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ ካለፉት 3 ቀናት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ አለመስማታቸውን ገልጸዋል። አርብቶአደሮቹ ትናንት ጥቃት እንደሚፈጽሙ ማስጠንቀቂያ ልከው የነበረ ቢሆንም፣
ዲመካ ከተማና አካባቢዋ ሌሊቱን በሰላም አሳልፈዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ፖሊሶች በብዛት ተሰማርተው እንደሚገኙም ነዋሪዎች ይገልጻሉ።