ሚያዝያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች የመስክ ጉብኝት በማድረግ ባወጡት ሪፖርት በሲቲ ዞን ባለፈው ወር ብቻ በተከሰተው ድርቅ ከ2 ሺ በላይ በጎችና ፍየሎች ሲያልቁ ነዋሪዎችም እየተሰደዱ ነው።
በረሃቡ ምክንያት በሃዲጋላ ወረዳ ጉርጉር ቀበሌ በጎች የሌሎችን በጎች ቆዳ ሲበሉ መታየታቸውን በስእል የተደገፈው ሪፖርት ያሳያል።
አይሺያ፣ ሃድሃጋላ፣ ከፊል ሽንሌ፣ ከፊል ደምበል፣ ሰሜን ኤረር፣ ከፊል አፍዴም እና መኢሶ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች ተብለው ተለይተዋል።
በሽንሌ፣ ሃዲጋላና አይሺያ ወረዳዎች እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው የቤት እንስሳት ያለቁ ሲሆን፣ ነዋሪዎችም ድርቁን በመሸሽ የተሻለ ምግብ ወደ ሚያገኙበት ቦታ ፈልሰዋል። በአንዳንድ አካባቢዎች ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል።
አለማቀፍ ማህበረሰቡ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በመሆን እርዳታ ለማድረስ ሙከራ እያደረጉ መሆኑን ሪፖርቱ ያሳያል።