ሚያዝያ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት አይኤስን ለማውገዝ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም በጠራው ሰልፍ ላይ ሁከትና ብጥብጥ አስነስተዋል የተባሉትና በወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ የሚገኙት ተከሳሾች ላይ መደበኛ
ክስ ተከፈተ።
በዚህም መሰረት የሚሊዮኖች ድምፅ ጋዜጣ አምደኛና የአንድነት አባል የነበረው ወጣት እስማኤል ዳውድን ጨምሮ በሌሎች 18 ተከሳሾች ላይ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባቸዋል።
በወንጀል ዝርዝሩ ላይ ተከሳሾቹ ‹‹ቤተ መንግስት አካባቢ በቡድን በመሆን መፈክር በመያዝና በቃል በመናገር “ተነስ! በለው!”ጊዜው ዛሬ ነው አትነሳም ወይ፣ የሞተው ሬሳ ያንተ አይደለም ወይ? መንግስቱ ሀይለማርያም ይምጣልን!
ከኢህአዴግ አይ ኤስ ይሻለናል!፣ ወያኔ ሌባ!፣ ውሸት ሰለቸን!፣ ዝምታ ይብቃ!፣ እናት ኢትዮጵያ ያደፈረሰሽ ይውደም!” በማለት ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረዋል ተብሏል።
እንዲሁም መፈክሮችን በመያዝ እና ወደ ፀጥታ ሀይሎች ድንጋይ በመወርወር ሰልፉን አውከዋል ያለው አቃቤ ህግ፤ “በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ወንጀል- በቡድን ስብሰባን በማወክ ወንጀል›› መከሠሳቸውን
አስረድቷል።
ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ያሉት ተከሳሾች ስድስት ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን፤ በሌሎቹ 14 ተከሳሾች ላይ ሁለት ክስ እንደቀረበባቸው የክስ ቻርጁ ያትታል።
ዐቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ 21 የሰው ምስክር 6 የሰነድ ማስረጃና ሁለት ኤግዚቢቶችንም አቅርቧል።
ከተከሳሾቹ ውስጥ ከ1ኛ ተከሳሽ፣ 2ኛ ተከሳሽ፣ 3ኛ ተከሳሽ፣ 6ኛ ተከሳሽ፣ 11ኛ ተከሳሽ 12ኛ ተከሳሽ የሰጡት የእምነት ቃል በሰነድ ማስረጃነት ቀርቧል።
በኤግዚበትነት “ከአባይ በፊት የህዝብ እንባ ይገደብ” እና “ዝምታ ይብቃ” የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ሳምፕሎችም በ ኤግዚቢትነት ተያይዘው ቀርበዋል።
ይሁንና ከሚያዚያ 20 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው ወጣት እስማኤል ዳውድ፣ ከትላንት በስቲያ ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ፒያሳ በሚገኘው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ
ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርቦ ዐቃቤ ህግ በሰነድ ማስጃነት ያቀረበው ቃል የእሱ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
‹‹የሰጠሁት ቃል የኔ አለመሆኑን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ 3 መርማሪዎች ከማረፊያ ቤት ሌሊት 7፡30 አካባቢ ጠርተውኝ እዚህ ወረቀት ላይ ባትፈርም እየተፈራረቅን እናድርብሃለን በማለት በከዘራ እየመቱ ያስረሙኝ መሆኑን
ፍርድ ቤቱ እንዲገነዝብልኝ›› ሲል እስማኤል ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አቅርቧል።
ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም በዋለው ችሎት በአንድ መዝገብ ውስጥ ከሚገኙት 19 ተከሳሾች ውስጥ ወጣት እስማኤልን ዳውድን ጨምሮ ሌሎች አራት ተከሳሾች በድምሩ አምስት ተከሳሾች የዋስትና መብት ተነፍጓል።
እንዲሁም አስራ አራቱ ተከሳሾች የተጠየቀባቸውና የዋስትና ገንዘብ ብር 10000 በሲፒኦ አሰርተው ገቢ ቢያደርጉም አቃቤ ህግ በጠየቀው ይግባኝ የተነሳ ተከሳሾቹ ገንዘቡን አስይዘው ወደ ማረፊያ ቤት እንደተመለሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡