ሚያዝያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሬውተርስ የግብጽ መንግስታዊ የዜና ማሰራጫን ጠቅሶ እንደዘገበው ፤ ሊቢያ ውስጥ ታግተው የነበሩና በግብጽ ጦር ጥረት ከታገቱበት የተለቀቁ 27 ኢትዮጰያውያን ዛሬ ሀሙስ ካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ገብተዋል።
ኢትዮጰያውያኑ በግብጽ አውሮፕላን ተጉዘው ካይሮ ሲደርሱ በግብጽ ፕሬዚዳንት በአብደል ፋታህ አል-ሲሲ እና በሌሎች ከፍተኛ የግብጽ ባለስልጣናት አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፤የአቀባበል ሥነ-ስር ዓቱ በግብጽ ሚዲያዎች የቅጥታ ስርጭት እንዲታይ ተደርጓል።
ይሁንና ከተመላሽ ኢትዮጰያውያኑ አንዱ እና ሌላ ሊቢያዊ የመረጃ ምንጪ_ ኢትዮጰያውያኑ ታግተው የነበሩት በሊቢያ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት እንደነበር ነው የተናገሩት።
አል ሲሲ በአንድ ሴሚናር ላይ ገለጻ ሲያደርጉ ግን ኢትዮጰያውያኑን ከታገቱበት አስለቅቆ ከሊቢያ በማውጣቱ ረገድ የግብጽ መከላከያ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ነው የተናገሩት።
የግብጽ ባለስልጣናት ዜናውን ያቀረበቡበት መንገድ ፣ ኢትዮጵያውዊው ስደተኛና የሊቢያ ባለስልጣን ከሰጡት መረጃ ጋር መጣረሱ፣ የዜናውን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ መክተቱን ረዩተርስ ዘግቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ወደ 800 ሰዎች በሞቱበት የሚዲትራኒያን ባህር አደጋ ከሞቱት ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ኢትዮጵያውያን መካከል 7 ወላጆች የልጆቻቸውን መርዶ ሰምተው ሀዘን ተቀምጠዋል።
አስደንጋጩን ዜና ከአደጋው በተረፈ ኢትዮጵያዊ በኩል ለቤተሰቦቻቸው እንዲነገር ተደርጓል። ሁሉም ሟቾች አባ ኮራን እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪዎች ነበሩ።